ፍቅሩ ኪዳኔ

0
907

‹‹የሱዳን ቡድን ሲመጣ የሱዳን ጋዜጠኛ አብሮ መጥቷል፣ ግጥሚያውን ለማስተላለፍ። እና ከስታድየም መስመር ይዘርጋልኝ ብሎ ይጠይቃል። ይሄኔ ፌዴሬሽኑ ኢትዮጵያ ራድዮ ጣቢያ ዋና ዳይሬክተር ጋር ይወድልና ይጠይቃል። እርሳቸው ደግሞ ሄደው፣ ያኔ የማስፋፊያ ሚኒስቴር ኃላፊ የነበሩትን አምደሚካኤል ደሳለኝን ይጠይቃሉ። (አምደ ሚካኤል የመጀመሪያው የስፖርት ኮንፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ ነበሩ)፤ እርሳቸውም ዘርጉላቸው አሉ።

ከዛ ለምን በአማርኛ አታስተላልፉም ብለው ጠየቁ። ‹እኛ የሚችል ሰው የለንም› የሚል መልስ ተሰጣቸው። ይድነቃቸውን ጠይቁት አሉና ደውለው ይድነቃቸውን ሲጠይቋቸው፣ አንድ ሰው አለ አሏቸውና ይዘርጋ ተብሎ መስመር ተዘረጋ። እኔም መደበኛ ፕሮግራም ለሰኞ ጠዋት አዘጋጅ ተብዬ ስታድየም ሄድኩኝ።

ትሪቡን ላይ ቁጭ ብዬ ጨዋታው እስኪጀመር እጠብቃለሁ። ኹለት ትንንሽ ጠረጴዛዎች እና ኹለት ድምጽ ማጉያዎች ተቀምጠዋል፤ ሜዳው ጋር። የሱዳኑ ከካርቱም መስመር ይጠብቃል መሰለኝ፤ የኢትዮጵያ ቦታ ላይ ግን ምንም ሰው የለም። በኋላ ጨዋታው ትንሽ ደቂቃ ሲቀረው በድምጽ ማጉያ ‹አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ በአስቸኳይ ይፈለጋሉ› ተባልኩ። ቦታዬን ያዙልኝ ብዬ ወረድኩ።

ጋሽ ይድነቃቸው ይጮኹብኛል፤ የት ነው የጠፋኸው ብለው። እኔ ማን ትናገራለህ ብሎ ነገረኝ አልኩኝ። ‹በል አሁን ጨዋታውን አስተላልፍ ተባልኩኝ።››

ከስምንት ዓመታት በፊት ፍቅሩ ኪዳኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ኳስን በሬድዮ ያተላለፉበትን አጋጣሚ በሚመለከት ከጋዜጠኛ ዮናስ ተሾመ ጋር ባደረጉት ቆይታ የተናገሩት ነው። ይህ አጋጣሚ የተፈጠረውም በ1943 በሱዳን እና ኢትዮጵያ መካከል የተደረገውን ጨዋታ ተከትሎ ሲሆን፣ በዚህም ፍቅሩ ጨዋታን በቀጥታ በሬዲዮ ማስተላለፍ የቻሉ የመጀመሪያው የስፖርት ጋዜጠኛ እንደሆኑ ይነገራል።

በስፖርት ጋዜጠኝነት ዘርፍ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆኑትና ጋዜጠኛ እንዲሁም ደራሲ ፍቅሩ ኪዳኔ በ88 የእርግና ዘመናቸው ባሳለፍነው ጥቅምት 01/2015 ማለዳ ላይ ዜና እረፍት የተሰማው።

ፍቅሩ ኪዳኔ የተወለዱት በ1927 አዲስ አበባ ከተማ ነው። አባታቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ነበሩ። ከአባታቸው ጋር የማይለዩት ፍቅሩ፣ ከአባታቸው ጋር ስታድየም ይሄዱ ነበር። በኋላም በእድሜ ከፍ ሲሉ የስፖርት መምህር ሆነው አገልግለዋል። ቀጥሎም በኢትዮጵያ ሬዲዮና የተለያዩ የአገር ውስጥ የሕትመት ውጤቶች ስለ አገር ውስጥ ስፖርት ዘገባዎችን ይሠሩ ነበር።

የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር በ1961 ሲመሠረት የመጀመሪያው ፕሬዝደንት ነበሩ፤ ፍቅሩ ኪዳኔ። እንዲሁም በብስክሌት ፌዴሬሽን፣ ቴኒስ ፌዴሬሽን እና በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በዋና ጸሐፊነት፣ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት በመሆን አገልግለዋል።

ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያገኘነው የሕይወት ታሪካቸው እንደሚያስረዳው፣ በዓለም ዐቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥም በአመራርነት፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የቀድሞ ፕሬዝደንት የነበሩት የኢሳ ሃያቱ አማካሪ ጭምር በመሆን ሠርተዋል።

ፍቅሩ ኪዳኔ በስፖርቱ ዓለም ምን ሠሩ ቢባል በጠቅላላ ሲጠቀስ፣ ከአዲስ አበባ ስታዲየም ኢንተርናሽናል የእግር ኳስ ግጥሚያን በራዲዮ ለመጀመርያ ጊዜ ያስተላለፉ፣ ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በተሳተፈችበት የሜልቦርን ኦሎምፒክ ከቡድኑ ጋር በጋዜጠኝነት አብረው የተጓዙ፣ የቀድሞው የዓለም ዐቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝደንት ኹዋን አንቶኒዮ ሳማራንጅ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር፣ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር በኮንጎው ዘመቻ የተሳተፉ፣ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ፣ የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ፣ የሸዋ ጠቅላይ ግዛት እግር ኳስ ሊግ ዋና ጸሐፊ የሚሉት የተወሰኑ ሆነው እናገኛቸዋለን።

ከ1969 ወዲህ ኑሮአቸውን አድርገው በቆዩበት በፈረንሳይ ፓሪስ ለሚገኘው እለታዊ የስፖርት ጋዜጣ ለኪፕ እና ሳምንታዊ የእግር ኳስ መጽሔት ፉትቦል ፍራንስ፣ ዶቼቬሌ (የጀርመን ድምፅ) እና ሌሎች የዓለም ዐቀፍ ታዋቂ መገናኛ ብዙኀን መሥራት ችለዋል።

ፍቅሩ ደራሲም ሲሆኑ፣ ‹የፒያሳ ልጅ› እና ‹የስፖርት ጨዋነት ምንጮች› የተሰኙ መጻሕፍትን ለአንባቢዎች ማድረስ ችለዋል።

ከአራት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ውስጥ የደመቀ ታሪክ ያላቸውን ባለውለታዎች ለማስታወስ አንድ ዝግጅት አዘጋጅቶ ነበር። በዚህም ዝግጅት ላይ ፍቅሩ ኪዳኔ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ እንዲሆኑ መመረጣቸው ይታወሳል።

ጋዜጠኛና ደራሲ ፍቅሩ ኪዳኔ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ነው በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት። ፍቅሩ የአንድ ልጅ አባት ሲሆኑ፣ ኹለት የልጅ ልጆችንም ዐይተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here