ሕክምና መቼ ተጀመረ ብሎ ዘመኑን ከነባለሙያው ማስቀመጥ ባይቻልም፣ ዘመናዊ የሚባለውና አሁን በስፋት ዓለማችን የምትገለገልበት የሕክምና ዘዴ ከጥቂት መቶ ዓመታት በላይ እድሜ እንዳላስቆጠረ ይታወቃል። በጊዜ ሂደት የልምድ ሐኪሞችም ሆኑ ባሕላዊ አካሚዎች ያካበቱትን ልምድ ለትውልድ በማስተላለፍ ዘመናዊና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተቀባዮቹ አሻሽለው የሚያክሙበት ዘዴ አሁንም ድረስ ውጤታማ እያደረገ ዘልቋል።
በተለያዩ አገራትና ሥልጣኔዎች ባህልንም ሆነ ልምድን አልያም እምነትን መሠረት ያደረጉ የሕክምናም ሆነ የፈውስ መንገዶች ቢኖሩም፣ እንደ አሁን ውስብስብና የተሳሰሩ የሆኑበት ዘመን እንደሌለ መገመት ይቻላል። አንዱ የሌላውን እውቀት በገንዘቡ እየሸመተ ከራሱም ጋር አዳቅሎና አስማምቶ ለትውልድ እያስተላለፈው ስለመጣ አሁን ሙያውን ለማካበት ዓመታትን የሚጠይቅ ሆኗል። ይህም ቢሆን እውቀቱ በአንድ ሰው ብቻ የሚቻል ባለመሆኑ ሐኪሞች ይበልጥ የሚያዳብሩትና ‹ስፔሻሊስት› የሚባሉበትን መስክ መርጠው ያጠናሉ።
ስለ ሕክምና ይህን ያህል ያልነው ‹ፕላሴቦ› ተብሎ በተለይ በሕክምና ባለሙያዎች ዘንድ ስለሚታወቅ የሕክምና አልያም የመዳን መንገድ በጥቂቱ ልንነግራችሁ ነው።
መድኃኒት ጥቅም ላይ መዋል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለማንኛውም ዓይነት ሰው ተመሳሳይ ውጤት እንደማያመጣ ይታወቃል። በሕክምናው ዘርፍ፤ የታካሚው እምነት ብቻ ሳይሆን የአካሚው አስተሳሰብም በሕክምናው ውጤት ላይ ተፅእኖ እንደሚያሳድር በተለይ በባለሙያዎቹ ዘንድ ይታወቃል። መርፌ ፍቱን ነው ብለው የሚያምኑ እናቶች እንደተወጉ ወዲያው ዳንን የሚሉት የእምነታቸው ጥንካሬ እንዳለ ሆኖ፣ ከሕክምናው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለው ‹የውሸት መድኃኒት› ሲሰጣቸውም የሚሻላቸው ጊዜ በርካታ ነው።
ፕላሴቦ እየተባለ የሚታወቀው ‹የውሸት መድኃኒት› አጠቃቀም፤ ታመምኩ ላለው ሰው ከሕመሙ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለውን ከረሜላም ሆነ ስኳርን ማስዋጥ ሊሆን ይችላል። ይህ በሕጻናት ብቻ ሳይሆን በአዋቂዎችም ላይ ውጤታማ የሚሆን የአስተሳሰብ ተፅእኖ እንደሆነ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ። ለዚህም ሲባል ሐኪሞች የሚያክሙትን ሰው ተስፋ በተቻላቸው መጠን ለመጨመርና የመዳን እድሉ ከፍተኛ እንደሆነ እንዲሰማው ሲጥሩ ይታያሉ።
ስለፕላሴቦ ተፅእኖ በርካታ ጥናት ላይ የተመረኮዘ መረጃ አለ። የሕክምና ባለሙያዎች በስፋት ስለማይናገሩ አንዳንዶችም ሙያውን ያራክሰዋል ብለው የሚያስቡ እስኪመስል ድረስ ስለፕላሴቦ ከመናገር ይቆጠባሉ።
“ፕላሴቦ ኢፌክት” እየተባለ ስለሚታወቀው ስለዚህ የሕክምና ሁኔታ ጽሑፍ ካቀረቡ መካከል ሄልዝ ኢሴንሻል አንዱ ነው። ምንም ዓይነት የአዳኝነት ንጥረ ነገር የሌለውን መድኃኒት ነው ብሎ በመስጠት እንደሚያድን አድርጎ በማሳመን የሚደረግ የሕክምና ዘዴ የእውነተኛውን መድኃኒት ያህል ውጤታማ እንደሚሆን ይጠቅሳል። ይህ ማለት የአእምሯችን እምነት ጥንካሬ የመድኃኒትን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ነው። ከመድኃኒት እኩል ሊሆን በሚችል መጠንም አስተሳሰባችንን ማጠንከሩ ለመዳን ያለንን ተስፋ እንደሚጨምረው ያመላክታል።
በሕክምናው ዘርፍ አዲስ መድኃኒት በምርምር ተገኝቶ ጥቅም ላይ ከመዋሉም ሆነ ወደ ገበያ ከመሰራጨቱ በፊት የተለያዩ ፍተሻዎችን ያልፋል። በእንስሳት ጀምሮ በሰው ልጆች ላይ ከተፈተሸም በኋላ ምን ያህል ውጤታማ እንደሚሆን ከተለያዩ ማነጻጸሪያዎች ጋር እያስተያዩ ይፈትሹታል። ከዚህ የማጣራት መንገዳቸው መካከል መድኃኒቱን ሲፈትሹ የሚያድን ብለው የሠሩትን ለተወሰኑ ሰዎች ከሰጡ በኋላ፣ ለተመሳሳይ ሰዎች ምንም ከበሽታው ጋር ግንኙነት የሌለውን የውሸት መድኃኒት አዘጋጅተው ለንጽጽር ለሌሎቹ ይሰጣሉ።
ለፍተሻ ተብሎ ‹የውሸት መድኃኒት› ከሚሰጣቸው መካከል እውነት መስሏቸው የሚድኑ በርካቶች መኖራቸው ነው ይህን ‹የውሸት መድኃኒት ተጽእኖን› ባለሙያዎቹ እንዲያውቁት ያደረጋቸው። ፕላሲቦ ኢፌክት በማለትም ልዩነቱን አጥንተው የውሸት መድኃኒት በመዳን ሂደት ላይ የሚያመጣውን ተፅእኖ ለማወቅ አስችሏቸዋል።
የውሸት መድኃኒት ተብሎ ለበሽተኞቹ የሚሰጠው የስኳር ወይም የጨው እንክብል አልያም ውሃ በሲሪንጅ ሊሆን ይችላል። ይህ መደረጉን የሚሰጣቸው ሰዎች እውነተኛው የተሰጣቸውም ሆኑ የውሸቱን የወሰዱት እንዲያውቁት አይደረግም። እነሱም ብቻ ሳይሆኑ የተመራማሪዎቹ አስተሳሰብና እምነትም ተፅእኖ እንዳያሳድር ሲባል፣ የትኞቹ ምን ዓይነቱን መድኃኒት እንደወሰዱ እንዲያውቁ አይደረግም። ይህ ቢሆንም ግን የውሸቱን ከወሰዱት መካከል እውነተኛው መድኃኒት እንደወሰዱት ውጤታማ የሚሆኑ መኖራቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ይህ የውሸት መድኃኒት እንዴት ውጤታማ ያደርጋል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሲሆን፣ የሕክምና ባለሙያዎች የተለያዩ ምክንያቶችን ያቀርባሉ። ታካሚው እድናለሁ ብሎ የመጠበቁ ሁኔታ፣ አልያም የመዳን ተስፋውና በሕክምናው ላይ የሚያሳድረው አመኔታ ሌላው መሠረታዊ መንስዔ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ መድኃኒቱን የሚቀበለው ሰው እምነት፣ ጥንካሬ እና የአስተሳሰቡ ውጤት በሰውነቱ ውስጥ እንዲመነጩ የሚያደርጋቸው ኬሚካሎች ይኖራሉ ይላሉ።
ይህ ውጤት አእምሯችን በሰውነታችን ላይ ካለው የገዘፈ ተፅእኖ ሳቢያ የሚመጣ ነው ተብሎ በባለሙያዎች ይነገር እንጂ፣ ፕላሴቦ የታማሚን ጤንነት የሚያሻሽልበት ትክክለኛው ምክንያት እንዳልታወቀ ይነገራል። ይህ በመሆኑም አሁን ድረስ ተፅእኖውን ለማወቅ ራሱን የቻለ ጥናት እየተደረገ እንደሆነ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።
አንድ ሰው እንደሚድን የሚሰጠው ተስፋና ስለመድኃኒቱም ሆነ ስለሕክምናው የሚኖረው የእምነት ጥንካሬ ለጤናው መሻሻል ቀጥተኛ ተፅእኖ ይኖረዋል። ይህ የሚሆነው ታማሚው ያድነኛል ብሎ ሲያምን ብቻ ሳይሆን፣ አያድነኝም ብሎ ያመነው እውነተኛ መድኃኒት ላይም ቢሆን አስተሳሰቡ ተፅእኖ ያሳድራል። ለዚህም ሲባል ታካሚዎች የሚኖራቸውን ተስፋ ለማሳደግና እንደሚድኑ ለማሳመን፣ ብሎም የእምነት ጥንካሬያቸውን ለማሳደግ የጤና ባለሙያዎች እንዲጥሩ የሚደረገው።
ለምሳሌ ያህል፣ ራስ ምታት አለብኝ ብሎ መድኃኒት የሚወስድ ሰው ድንገት አሞት መድኃኒት ሲወስድ ወዲያው የሚድንበት አጋጣሚ አለ። ንጥረ ነገሩ ከሠውነቱ ተዋሕዶ ፍቱን እስኪሆንለት ሳይጠብቅ የቀደመ ትውስታው እምነቱን ስለሚያጠነክርለት ገና እንደዋጠው ሊሻለው ይችላል። በዚህ ምክንያት በውሸት መድኃኒት የሚያገግሙ ሰዎች ቁጥራቸው ከአጠቃላዮቹ ግማሽ የሚሆኑት እንደሚሆኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በጎ ውጤት ተመኝተው ጥሩ ውጤት የሚያመጡ የመኖራቸውን ያህል ክፉ እንደሚደርስባቸው አስበው ጥሩ ያልሆነ ውጤት የሚያገኙም አሉ። እነዚህም ‹ኖሲቦ ኢፌክት› እየተባለ አስተሳሰባቸውና የጤና ሁኔታቸው ይገለጻል። ይህ ቢሆንም ግን እስካሁን የውሸት መድኃኒት በመስጠት የሚካሄደው የሕክምና መንገድ ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንደሚያመጣ አልታወቀም። ለወደፊት በምርምር እስኪረጋገጥ ድረስ ግን የአእምሯችንን ጥንካሬ በመጠቀም እምነታችንንም በማጎልበት ልንጠቀምበት እንደሚገባ እስከዛሬ በታወቀው መጠን ድረስ መናገር እንደሚቻል ነው።
የፕላሲቦ ተፅእኖን ብዙዎች ሥነልቦናዊ (ሳይኮሎጂካል) ነው በማለት ከአስተሳሰብ ጋር የተገናኙ ራስ ምታትን የመሳሰሉ ሕመሞችን ለማዳን የሚውል ነው ቢሉም፣ አካላዊ (ፊዚካል) የሚባሉ ከሰውነት አካል ጋር ወይም ከበሽታ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሕመሞችንም እንደሚያሻሽሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ሜዲካል ኒውስ ቱዴይ ስለፕላሲቦ ባስነበበው ዘገባ መሠረት፣ የዚህ የውሸት መድኃኒት ውጤታማነት ከሺሕ በላይ በሚሆኑ የቤተሙከራ ምርምሮች የተረጋገጠ ነው። በሥራ ላይ ያሉ በርካታ የሕክምና ባለሙያዎችም ለታማሚዎች እነዚህን የውሸት መድኃኒቶች እንደሚሰጡና ውጤታማ እንደሚሆኑ መናገራቸውን ድረ ገጹ አስፍሯል።
በተለያዩ ምርምሮች እንደተረጋገጠው የመድኃኒቱ ይዘት ብቻ ሳይሆን ቀለሙና መጠኑም በሰው ልጆች የመዳን ሁኔታ ላይ ተፅእኖ ያሳድራል። እንደሚያድን የሚያውቁት የመድኃኒት ቀለም ያለው ሲሆን፣ አልያም ቅልቅ መድኃኒቶች ውጤታማ እንደሚያደርጉ የሚያምኑ በርካቶች መሆናቸው በባለሙያዎች ያታወቃል።
በዚህ ምክንያት አዳዲስ መድኃኒቶች ሲመረቱ ለሙከራ የውሸትና የእውነቱን መድኃኒት መስጠቱ ብቻ በቂ ስላልሆነ ምንም ዓይነት መድኃኒት የማይወስዱ ሦስተኛ ቡድን ፈታሾች እንዲኖሩ ይደረጋል። በዚህ መንገድ አንድ መድኃኒት ፈቃድ የሚያገኘው ከፕላሲቦው በበለጠ ውጤታማ ማድረጉ ሲታወቅ ነው።
የፕላሲቦ ተጽእኖ እንደወሳጁ የእምነት ጥንካሬም ሆነ አስተሳሰብ ቢለያይም፣ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በተለያዩ ሰዎች ላይ ተመሳሳይ ውጤት ያስከትላል። ለምሳሌ፣ በእንክብል ከሚሰጥ ይልቅ በመርፌ የሚወጋውን ብዙዎች ፍቱን አድርገው ስለሚወስዱት የበለጠ እንደሚያሽላቸው ታውቋል።
ቤተር ሄልዝ የተባለ ሌላ ድረ ገጽ በሰፊው ስለፕላሲቦ ያተተ ሲሆን፣ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ ይላል። ውጤታማ ማድረጉ እንዳለ ሁኖ ሰውን ዋሽቶም ቢሆን ማዳኑ ከሕክምና ሥነምግባር ውጪ ነው በማለት የሚሞግቱ መኖራቸውን ቢጠቅስም፣ ይህን አመለካከት ውድቅ በማድረግ ዋናው ታማሚው እንዲሻለው ማድረጉ ነው በማለት መንገዱን ብዙዎች እንደሚስማሙበት ይጠቅሳል።
ዋናው የአስተሳሰብ አድማሳችንን በማስፋት እምነታችን እንዲጠነክር በማድረግ በባዶ እንዲሻለን በማድረግ ማከም ከተቻለ፣ እምነታችንን ተጠቅመን በራሳችን ቢያንስ ትንንሽ ሕመሞችን ማስታገስ እንደሚቻለን አመላካች ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015



