በዘውዳዊው የኢትዮጵያ የአገዛዝ ሥርዓት መሪዎች ከራሳቸው ባልተናነሰ በፈረሶቻቸው ሥም መጠራት የተለመደ ነበር። አባ ታጠቅ – አፄ ቴዎድሮስ ፣ አባ በዝብዝ – አፄ ዮሐንስ፣ አባ ዳኘው – ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፣ አባ ጠቅል – አፄ ኃይለሥላሴ እያሉ ከብዙ በጥቂቱ መጥቀስ ይቻላል። ይህም ፈረሶች እንዲሁም ሌሎች የጋማ ከብቶች በኢትዮጵያዊያን የቀን ከቀን ኑሮ ውስጥ ጉልህ ቦታ እንዳላቸው ማሳያ ነው።
በፈረስ፣ በቅሎ እንዲሁም በአህያ ጋሪዎች ተሳፍሮ መንቀሳቀስ፣ እህል ወይም ሌላ ዓይነት ጭነት መጫን የተለመደ ነው። በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል የግለሰብ ሀብት ከሚለካባቸው መስፈርቶች አንዱ ግለሰቡ ያሉት የከብቶች ቁጥር ነው። በዚህ ቁጥር ውስጥም ምንም እንኳን የቀንድ ከብቶች ቀዳሚ ተጠቃሽ ቢሆኑም የጋማ ከብቶች ብዛትም የግለሰቡን የሀብት ልኬት ይወስናሉ።
ይብዛ በሚባል አባይ በረሃ ውስጥ በሚገኝ የገጠር ቀበሌ የሚኖሩ ተግባር ይሁኔ የሚባሉ አርሶአደር ሲናገሩ፣ ‹‹የእህል ወፍጮ ለማግኘት ከቤቴ ተነስቼ የኹለት ሰዓት የእግር መንገድ መጓዝ ግድ ይለኛል። የመንገዱ አብዛኛው ክፍል ደግሞ ተራራማ ስለሆነ በዚህ መንገድ ተሸክሞ ለመጓዝ አስቸጋሪ ነው።›› ይላሉ።
ታዲያ በዚህ አስቸጋሪ መንገድ ለወፍጮ ወይም ለገበያ የሚሄድን እህል መሸከም የአህያዎች ሥራ ነው። ‹‹አህያ ባይኖረኝ በልቶ ማደር አዳጋች ይሆንብኝ ነበር። በነሱ ላይ ነው እህላችንን ለገበያም ለወፍጮም የምናደርሰው።›› የሚሉት ይሁኔ፣ ከነሱ በባሰም በእግር እስከ ስድስት ሰዓት ከሚወስድ መንገድ እህል እንዲሁም ሌላ ጓዞችን በመሸከም ባለቤታቸውን ማገልገል ግድ የሆነባቸው አህዮች እንዳሉ ይናገራሉ።
አህያዎች ሲደክሙና የተለመደውን አገልግሎታቸውን መስጠት ሲያቆሙ ባለቤቶቻቸው ከቤት ሲያስወጧቸው መመልከት የተለመደ ሲሆን፣ በተለይ የጋሪ ፈረሶች አገልግሎት በሚሰጡበት ዘመናቸውም ከቤት ውጭ እንዲያድሩ የሚደረጉበት ጊዜ በርካታ እንደሆነ ይነገራል።
ይሁኔ እንደሚሉትም፣ እርጅና የተጫጫናቸውን አህዮች ለመሸጥ የሚሞክሩ ሲሆን ካልተሳካላቸው ግን እያዘኑም ቢሆን ከቤት ለማስወጣት እንደሚገደዱ ገልጸዋል። እንደ ምክንያት ሲያነሱም አህዮቹ ከደከሙ በኋላ በበሽታ የመጠቃት እድላቸው ከፍተኛ ስለሆነ ለሌሎች እንስሳትም ጠንቅ እንዳይሆኑ ከማሰብ የተነሳ እንደሆነ ገልጸዋል።
ለዓመታት ሲገለገሉበት የቆዩትን ፈረስ በእርጅናና በሕመም ምክንያት የተለመደውን አገልግሎት መስጠት ሲያቆም፣ ከቤት ማስወጣት ተመልሶ ከመጣም ራቅ ወዳለ ቦታ ወስዶ እንዳይመለስ ዐይኑን ማጥፋትን የመሰሉ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ይሰማል። በዚህም ምክንያት ባለቤት አልባ የጋማ ከብቶችን መመልከት ያን ያህል የሚያስገርም ጉዳይ አይደለም።
የጋማ ከብቶችና ሕክምና
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ሕክምናና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ሽመልስ ዳኛቸው (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ምንም እንኳን የእንስሳት ሐኪሞች የጋማ ከብቶችን ለማከም በቂ እውቀት ያላቸው ቢሆንም፣ የመድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎች አቅርቦት ችግር እንዳለ ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም በከብቶቹ ባለቤቶች በኩል የግንዛቤ ችግር እንዳለ ይናገራሉ። እንደማንኛውም እንስሳት የጋማ ከብቶችም አስፈላጊ የሕክምና እርዳታ ማግኘት አለባቸው የሚሉት ሽመልስ፣ የጋማ ከብቶች ሲታመሙ ወደ ሕክምና ተቋማት መውሰድ የተለመደ አይደለም ብለዋል።
ከውጭ አገራት የሚገቡት ለጋማ ከብቶች ሕክምና የሚያገለግሉ መድኃኒቶችና የሕክምና መሣሪያዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖራቸው ሕክምናው ላይ ከፍተኛ ችግር የፈጠረ ሲሆን፣ ከብቶቹ መታከም የማይችሉ እስኪመስሉ ድረስ ሕክምናው ያለበት ደረጃ ዝቅተኛ እንደሆነ ሽመልስ ተናግረዋል። ከክትባት ጀምሮ የጸረ ተዋህሳት መድኃኒቶች እንዲሁም የሕመም ማስታገሻዎች በአገር ውስጥ የማይመረቱ እንዲሁም በመንግሥትም ትኩረት ተሰጥቶት ከውጭ እንዲገቡ የማይደረጉ ናቸው።
የጋማ ከብት ባለቤቶች ለከብቶቹ አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረግ፣ ወደ ሕክምና ተቋማት መውሰድ እንዲሁም ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ሥራዎችን እንዳይሠሩ ማድረግ ቢገባቸውም፣ ይህን ካለማድረግ የተነሳ በከብቶቹ ላይ የጤንነት መጓደሎች ይስተዋላሉ።
እርጅናና ሕመም ያጠቃቸውን ከብቶች ከቤት ማስወጣት
ምንም እንኳን ይህ ችግር በሌሎች እንስሳትም ላይ የሚስተዋል ቢሆንም በጋማ ከብቶች ላይ በስፋት ያለ ትልቅ ችግር ነው። የእንስሳት የባለቤትነት ምዝገባ ባለመኖሩ ከቤት ውጭ ለሚጣሉ እንስሳት ኃላፊነት የሚወስድ ግለሰብ ማግኘት ከባድ ነው የሚሉት ሽመልስ፣ በኢትዮጵያ የእንስሳት የባለቤትነት ምዝገባ መጀመር አለበት ይላሉ።
የጋማ ከብቶች በእርጅና ዘመናቸው የሚሰጡትን አገልግሎት ይቀንሳሉ። ይህም ተፈጥሯዊ ሲሆን፣ የከብቶቹ ባለቤቶች ያረጁና የታመሙ ከብቶችን ኃላፊነት መውሰድ እንደሚገባቸውም ይነገራል። ይሁንና ይህንን ኃላፊነት ካለመወጣት የተነሳ በርካታ የጋማ ከብቶች በእርጅና ዘመናቸው ኑሯቸውን በጎዳና ላይ እንዲያደርጉ ይገደዳሉ።
ይህንን የሚገድብ ሕግ እየተዘጋጀ እንደሆነ የሚጠቅሱት ሽመልስም፣ የእንስሳት የባለቤትነት ምዝገባ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል። ምክንያቱን ሲያስረዱም፣ በሕግ አግባብ ልክ ያልሆነ ሥራ የሚሠሩ ወገኖችን ተጠያቂ ለማድረግም ቢሆን የእንስሳቱን ባለቤት ማረጋገጥ ግድ እንደሚል አስረድተዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተሞክሮ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ሕክምና እና ሳይንስ ኮሌጅ ስፓና (SPANA) ከሚሰኝ በእንስሳት ዙሪያ ከሚሠራ መንግሥታዊ ያልሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ከሦስት ዓመታት በፊት ጀምሮ በጋማ ከብቶች ሕክምና እንዲሁም የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ በመሥራት ላይ ይገኛል።
በጎንደርና በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች ያሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አመራሮች፣ የእንስሳት ሕክምና ባለሙያዎች እንዲሁም የጋማ ከብት ባለቤቶችን ያካተተ ተከታታይ ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል። ሥልጠናዎችም የጋማ ከብቶችን ከርሀብ፣ ከሕመም፣ ከፍርሀት እንዲሁም ከጉዳት መጠበቅ እንደሚገባ ግንዛቤ በማስጨበጥ ላይ ያተኩራሉ።
የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከጋማ ከብቶች በርካታ አገልግሎቶችን እንደሚያገኝ የሚያነሱት ሽመልስ፣ በከብቶቹ ጤንነት ዙሪያ ከፍተኛ የግንዛቤ ችግር እንዳለ ገልጸዋል። ከስፓና ጋር በመተባበር እየተሠራ ያለው ሥራም ይህን ግንዛቤ ከፍ ማድረግ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሕክምና እና ምርምር
ለእንስሳቱ ሕክምና የሚያግዙ መድኃኒቶችንና መሣሪያዎችን በማቅረብና፣ በሕክምና መዳን የሚችሉ እንስሳትን በማከም ላይ ያተኮሩ ሥራዎች በመሠራት ላይ ይገኛሉ። በሕክምና መዳን የማይችሉ ከብቶችንም ስቃዩ በቀነሰ መንገድ በሰላም የማሳረፍ (Euthanasia) ሥራም እንደሚሠራ ሽመልስ ተናግረዋል።
በፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ኹለት ዓመታት ለጋማ ከብቶች ነጻ ሕክምና ይሰጥ የነበረ ሲሆን፣ በዚህ የነጻ ሕክምና ምክንያትም በርካታ ከብቶች ተጠቃሚ ሆነዋል። ባለፈው አንድ ዓመት ደግሞ የከብቶችን የሕክምና ወጪ በከፊል ባለቤቶቻቸው እንዲፈጽሙ የተደረገ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት ፕሮጀክቱ ከተጠናቀቀም በኋላ ከብቶችን ወደ ሕክምና ተቋማት የሚወስዱ የከብት ባለቤቶችን ማፍራት ተችሏል ተብሏል።
አሁንም ቢሆን የተወሰኑ የክትባት እንዲሁም የመድኃኒት ዓይነቶች በነጻ የሚሰጡ ሲሆን፣ በቀጣዮቹ ኹለት ዓመታትም ይህ ድጋፍ ቀጣይነት አንደሚኖረው ሽመልስ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጓዳኝ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ሕክምና እና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራንና ተማሪዎችን ያሳተፈ የጥናትና ምርምር ሥራዎች በመሠራት ላይ ይገኛሉ። በዚህም በአካባቢው ያሉ ፈረሶችን በብዛት የሚያጠቃውን የፈረስ ልክፍት በሽታ ለይቶ የመቆጣጠር ሥራ ተሠርቷል ተብሏል። ተማሪዎችም በሚማሩበት ጊዜ በእንስሳቱ ጤንነት አሳሳቢነት ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ይደረጋል።
ከስፓና ጋር በመተባበር ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመሥራት ላይ ያለው የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ሲሆን፣ ምንም እንኳን የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ግምገማ ባይደረግም፣ በዐይን የሚታዩ ለውጦችን ማምጣት እንደተቻለ ሽመልስ ተናግረዋል። በዚህም የሕመም ስሜት ያላቸውን ከብቶች ወደ ሕክምና ተቋማት መውሰድ እየተለመደ እንደሆነ ጠቅሰው፣ የጋማ ከብቶችም እንደሌሎች እንስሳት መታከም ይችላሉ የሚለውን ግንዛቤ በሰፊው መፍጠር እንደተቻለ ተናግረዋል።
በቀጣዮቹ ኹለት ዓመታትም ፕሮጀክቱ ጤናቸው የተጠበቀ የጋማ ከብቶች አንዲኖሩና ማኅበረሰቡም የእንስሳቱን ጤና ለመጠበቅ ቁርጠኛ የሚያደርገውን ግንዛቤ እንዲያገኝ ለማድረግ እንደሚሠራ ሽመልስ ተናግረዋል።
የመንግሥትና የኅብረተሰቡ ሚና
መንግሥት የጋማ ከብቶችን ጤና ለመጠበቅ የሚያገለግሉ አስፈላጊ መድኃኒቶችንና የሕክምና መሣሪያዎችን በበቂ መጠን ማስመጣት ይጠበቅበታል ያሉት ሽመልስ፣ የግል ባለሀብቱም ይህንን ሥራ ሊደግፍ እንደሚገባ ተናግረዋል። ከሕክምና ግብዓቶች በተጨማሪም የጋማ ከብቶችን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የእንስሳት ጤና አጠባበቅና ባለቤትነት በሕግ አግባብ የሚደነግግ አሠራር ያስፈልጋል ብለዋል። ይህንንም መንግሥት እየሠራበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በየአካባቢው ያሉ የሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም የእንስሳት ጤንነት አጠባበቅ ላይ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የጠየቁት ሽመልስ፣ አብዛኛው ችግሮች ከግንዛቤ እጥረት ምክንያት የሚነሱ እንደሆኑ ጠቁመዋል።
የትምህርት ተቋማት ከማስተማር ባለፈ የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባቸው ይታወቃል። በዚህ ረገድም ኃላፊነታቸውን በመወጣት የማኅበረሰቡን ግንዛቤ እንዲሻሻል ማድረግና የጥናትና ምርምር እንዲሁም የሕክምና ሥራዎቸን ሊሠሩ እንደሚገባ ሽመልሰ የዩኒቨርሲቲያቸውን ልምድ በማንሳት ተናግረዋል።
ከኹሉም በፊት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የከብቶቹ እንክብካቤ ላይ እንደሆነ የገለጹት ሽመልስ፣ ከብቶችን በመንከባከብና ያለ እድሜያቸው እንዲያረጁ የሚያደርገውን ከአቅም በላይ የሆነ ሥራ ባለማሠራት ጤንነታቸውን መጠበቅ እንደሚቻል ተናግረዋል። በተለይም የማጓጓዣ አገልግሎት የሚሰጡ ፈረሶችም ሆኑ በቅሎዎች ላይ የሚደርሰውን የሥራ ጫና ተመጣጣኝ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል። የታመሙ ከብቶችንም ወደ ሕክምና ተቋማት በመውሰድ ተገቢውን እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ ከኅብረተሰቡ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015



