የታገቢኛለሹ ጥያቄ

0
2054

ከሠሞኑ መነጋገሪያ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል የብዙዎችን ትኩረት የሳበው አንድ የአደባባይ የ‹ታገቢኛለሽ ወይ?› ጥያቄና መልሱ ነበር። ተጠያቂዋም ሆነ ጠያቂው ወጣቶች ሲሆኑ ጠያቂው የመረጠው በርካታ ታዳሚ የሚገኝበትን አገልግሎት መስጫ ቦታን ነው።

እንደታሪኩ አወራረድ ከሆነ ወጣቱ ለትዳር ትሆነኛለች ብሎ በሐሳቡ ያጫትን ሴት እውቅና ለማግኘትና ቀለበት ለማጥለቅ ያስብና ከጓደኞቹ ይማከራል። ድርጊቱ የተከናወነበት ምግብ ቤት ድንገት ሊጠይቃት ይስማማና ጓደኞቹ ደስታውን እንዲጋሩለትና ሂደቱን በምስል እንዲያስቀሩለት ይጋብዛቸዋል።

ተጠያቂዋን እንስትም ቀጥሮ ሲጠባበቁ ቆይተው ስትደርስ ገና ቁጭ ሳትል ይቀበላታል። የጋብቻ ጥያቄውንም ሲያስከትልባት የተደናገጠችው ወጣት እንዴት በሚል አስተያየት ስለግንኙነታቸው ደረጃ በመጠየቅ እንደማይሆን አስረግጣ ትነግረዋለች። ወጣቱም አልሸነፍም ባይ ይሆንና በልመና ማለት በሚቻል መልኩ ለመንበርከክ ወደምድር ይወርዳል።

በወጣቱ ድርጊት እጅግ የተቆጣች የምትመስለው ተጠያቂ ምንም እንዳልጠበቀች መገመት ቢቻልም፣ ጠያቂው ግን እምቢታዋን ፈጽሞ የጠበቀው አይመስልም ነበር። የእሷን ይሁንታ እንዲያገኝ አጃቢዎቹና የምግብ ቤቱ ታዳሚዎች በጭብጨባ ሊያግዙት ቢሞክሩም፣ የሁሉንም ትኩረት እንደያዙ የገባት እንስት ለመውጣት ትሞክራለች። ከተወሰነ ልምምጡ በኋላ አሻፈረኝ ብላ ጥላው ትሄዳለች።

ሂደቱን ተከታትለው እየወጡ የነበሩ ሌሎች ጥንዶች በር ላይ ሲያፅናኑት  ወደቀልቡ መለስ ያለ የሚመስለው ወጣት፣ ገባ ብሎ የሚጠብቁትን በምስልም የሚቀርፁትን ፊት ማየት ሲሳነው መሬት ቁጢጥ ብሎ አንገቱን ሲደፋ ቀረፃው ይቋረጣል።

የጥየቃውን ሂደትና እምቢታውን የተመለከቱ በርካቶች በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ አስተያየት ለመስጠትና ምስሉን ለመቀባበል ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር። አንዳንዶች እንዴት ትንሽ ፍንጭ ሳያገኝ እንድትጠረጥርም ሳያደርግ እንዲህ ያደርጋል ያሉ ሲሆን፣ እንደሌሎች ጥንዶች ለታይታና ለድራማ ውጤቱን እያወቁ ከሚደረግ ይህ ይሻላል ያሉ ነበሩ።

በአደባባይ ማድረግ ለምን አስፈለገ፣ ከባሕላችን ያፈነገጠ ነገር ድሮም ውጤቱ አያምርም ያሉ በርካቶች ናቸው። ምናለ ሕዝብ ፊት እሺ ብላ በኋላ ለብቻው እምቢ ብትለው ከመዋረድና ጉዳት ታድነው ነበር ያሉም ነበሩ። የውሸት ድራማ እንዳይሆን፣ ፕራንክም ነው ብለው በሚዲያ ሊመጡ ይችላሉ ያሉ ሲኖሩ እውቅና ለማግኘትም ሊሆን ይችላል ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ አሉ።

‹‹አድራሻውን ፈልጉልኝ እኔ አገባዋለሁ›› ብለው ለማፅናናት የፈለጉ እንስቶች፣ ‹‹ቆይ ታያለች ማንም አያገባትም!›› እያሉ የልጅቱን ፍላጎት ለመጫንና ሌሎች ሴቶች እምቢ እንዳይሉ ማስፈራሪያ አዘል የሚመስል አስተያየትም የሰጡ ነበሩ።

ከሁሉ ከሁሉ ለወደፊት እንዲህ እንደፊልሙ ዓለም ለመጠየቅ የሚያስቡትን የሚያስጠነቅቅና ቆም ብለው እንዲያስቡበት የሚያደርግ ነው ተብሏል። የጋብቻ ጥያቄን በአደባባይ ማድረጉ ጫና ለመፍጠር ካልሆነ ዓላማው ምንድን ነው ብለው ለጠየቁም ምላሽ የሰጣቸው የለም።

ስለወጣቶቹ የወደፊት ሕይወት መቀየር ብዙዎች አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ አንዳንዶች ደግሞ ሲሳለቁበት ታይተዋል። መንበርከክ ለፈጣሪ እንጂ ለትዳር አይገባም ያሉም በርካቶች ናቸው።


ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here