በድሉ አበበ በአበባ የሺጥላ (ዶ/ር) የተዘጋጀውን ‹እግዜር ቅኔ አማረው› የተሰኘውን የግጥም ስብስብ መጽሐፍ ቃኝቷል፡፡ ከመጽሐፉ የሽፋን ገጽ ጀምሮም፣ በመጽሐፉ የተካተቱ አንዳንድ ግጥሞችን በመጥቀስም በአቀራረብ እና በታዩ የፍልስፍና ይዘት ባላቸው ሐሳቦች ላይ እንደሚከተለው ዕይታውን አካፍሏል፡፡
እነሆ ዛሬ ለዳሰሳ የመረጥነው የግጥም ስብስብ መጽሐፍ ‹እግዜር ቅኔ አማረው› ይሰኛል። ደራሲዋ ዶ/ር አበባ የሺጥላ ናት። ከዚህ በኋላ አበባ እያልኩ እንደምቀጥል እየገለጽኩ አንባቢዎቼንም እርሷንም ይቅርታ በመጠየቅ ነው።
‹እግዜር ቅኔ አማረው› መጋቢት 2004 የታተመ የግጥም መድብል ነው። ስድሳ ስድስት ግጥሞች በ102 ገጾች ቀርበዉበታል። ይህም ምስጋናና አሁንም ምስጋናን ሳይጨምር ማለት ነው። ርዕሱ እኔንም ረብሾኛል። እግዜር የቅኔው ፈጣሪና አባት፤ እግዜር ቅኔው ጭራሽ ቅኔ አማረው ትለናለችና አበባ? ቅኔው ራሱ ነው ወይስ እኛ ነን ቅኔው?
አበባ ‹እኔኮ…› አለች ‹የሱ ቅኔ ነኝ። ስንት ዓመት የጻፈኝ፤ ማንም እንዳሻው የማይተረጉመኝ፤ ማንም እንደገባው እየተነሳ የእንዲህ ነሽ ‘ማይለኝ? ሁሉን ለመረዳት ፈጣሪው እሱ ነው፤ ቅኔ ደግሞ እኔ ነኝ። ምክንያቱም እኔ ቅኔ ነኛ በቃ!› ያለች ይመስለኛል። ወይም ደግሞ ‹ይሄ የምታነቡት ግጥም የኔ አይደለም። በቃ ሰጪውን፤ እግዜሩን ጠይቁት።› ያለችም ይመስለኛል። እደግመዋለሁ! እኔ ቅኔው ተሰጥቶኝ ነው ያለችም ይመስለኛል፤ ራሴም ቅኔ ነኝ ያለች ይመስለኛል፤ አስባችሁታል?።
የገጹ ሽፋን
የግጥም ስብስብ መጽሐፍ የጽሑፍ ቀለም ”እግዜር” ና “አማረው” በነጭ ፤ “ቅኔው” በቀይ ቀለም ተጽፈዋል። የሽፋን ስዕሉ ስስና ሳቢ ነው። አንዲት እንስት በቀኝ እጇ የተከፈተ መጽሐፍ ይዛለች። መጽሐፉ ላይ የሚታየው ስዕልም “ እግዜር ቅኔ አማረው” ይላል። በአንድ ትልቅ ነጠላ /እንበለው/ ፤ ነጠላውም ከቀኝ ትክሻዋ ወደ ቀኝ ትከሻዋ አልፎ በወገቧና በጭኗ ዞሮ ነጠላው ሙሉ በሙሉ በነፋስ ተለቋል።
ነፋሱ ኃይለኛ ይመስላል። ለዚህም ማሳያው ነጠላው ሙሉ በሙሉ ተዘርግቷል። ስስ ሰማያዊ ቀለም ነጠላውን ኹለት ቦታ በመሃል ያልፈዋል። አስራ ኹለት ጥለት መሳይ ስስ ቀይ፣ የዳይመንድ› ቅርጽ ያላቸው ጥለቶች ከኋላ ከተበተነው ነጠላ ጫፍ ላይ ይታያሉ። መጽሐፉን በቀኝ እጇ ይዛ ዐይኗን ወደ ላይ አቅንታ ጭኗን በግራ እጇ ሸፍና ለሰማዩ ታሳያለች።
እንዲህ እያለች ይመስለኛል፤ ‹‹የሰጠኸኝን ቅኔ ይኸው መልሼ ሰጠሁህ ተቀበል።›› ከጀርባው ላይ ፊደላት አንድም ብዙም ሆነው ነጭ ጠቃጠቆ ይታየኛል! የቆመችው ወይን ላይ ይሆን እንዴ? እግዜር ቅኔ አምረው/ የሽፋን ስዕሉ ሐሳብ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ በ”እንደ መግቢያ” በተሰኘው ግጥማ ላይ እንደዚህ ተገልጿል፦
“ እግዜር ቅኔ ሲያምረው፤
ገጣሚን ፍቅር ያሲዛል፤
ገጣሚስ ምን አቅም አለው?
‘ተያዘ’ አለው በቃ ይያዛል፤
ብእር ቀለሙን ይቀርጻል፤
አንዲት ፋሽኮ ወይን ይገዛል
ቀና ብሎ….
ልክ እንደዚህ ሰማይ ያያል
ይገረማል
በጥልቀቱ….
በስፋቱ….
በርቀቱ….
…
እግዜርስ ?
ለፍርድ ቀን የደበቃት የክት ዙፋኑን ያወጣል፤
ቅኔ ሊሰማ ይቀመጣል፤
ገጣሚስ ምን ይጽፋል?
ይህንን ማንበብ የሚሻ
ወደ ቀጣዩ ገጽ ያልፋል።
አበባ በግጥም ስብስቧ በአጠቃላይ ስለ ላጤነት፤ አብሮነት፤ ውበት፤ ፍቅር፤ እምነት፤ ሴትነት፤ ማኅበረሰብ፤ ሃይማኖት፤ አገር፤ እውቀት፤ ዕድሜ፤ ክብር፤ ፍልስፍና፤ ግጥም፤ ስጋት፤ ዘመንና ዘመንን መዋጀት፤ በሽታና ሌሎችንም በሚገባ ተቀኝታዋለች።
ስለ ፍቅር
በአንድ ግጥሟ ፍቅርን ከማፍቀር በፊት፣ አፍቅራም፣ ካፈቀረችም በኋላ ተቀኝታዋለች። በተለየ መንገድ በተለየ ዕይታ ዐይታዋለች፤ በሦስት ዘመን ማለት ነው። የመጀመሪያውን ጊዜ ‹ቅድመ አንተ› ነው የምትለው፤ እሷ። እንዲህ እያለችም ትመክረዋለች፤ የመጀመሪያውን ዘመን፦
“….ወዮ ወንደላጤ በጸሎትህ ጽና
የቀበሯት አጥንት የማናችን እንደሁ አላወቅንምና”
ቀድመን እንዳልነው ይሄ ሦስት ዘመንን የታከከ አንድ ግጥሟ ነው። ከዚያም ከቅድመ አንተ የ ‹እርሱና የርሷ› የአብሮነት ዘመን ይከተላል። ካለመታወቅ ወደ መታወቅ ትመጣለች። ከማወቋ በፊት /ቅድመ እርሱ/ ሦስት ነገሮች ያስፈሯት ነበር። እነሱም የልብ ስር ብርድ፤ አፍቃሪ የማጣት ሕመም እና እሳት። ሰው ካላፈቀረ አያመውም አይደል? ፍቅሩ ራሱ ሕመሙ ካልሆነ ማለቴ ነው፤ እንጃ!
ኹለተኛው ዘመን ይከተላል። ያም ዘመን ‘ከርሱ ጋር’ ይሰኛል። ያኔ ‹ቀራንዮን የመሰለ ሕመም› በቃል ይፈወሳል። ብርድ፣ ነፋስና ዝናብ ያገኟታል። እነዚህ ሕመም፤ ነፋስና ዝናብ በሽታዎቿ በሱ ፍቅር ይታከማሉ። ዋዕዩ እሳት ብሶቷን ይቀበላታል። እሷም በብዙ ‹አታልቅሺ በቃ›ዎች ብብቱ ስር ስትገባ ለቅሶዋ ይጠፋል። ከዚያም ሦስተኛው ዘመን ይጀምራል፤ ያም የድኅረ አንተ ዘመን ማለት ነው። ይሄ ዘመን አፍቃሪነት የተሞከረበት፣ የሕይወት ልምድ የተወሰደበት፣ ተወስዶም ልምድ የተገኘበት ምናልባትም በኹለት መንገድ። ነገር ግን ኋላን የረሳ የሚመጣን ለማስተናገድ ያለመ ልብ ነው። ለቅሶም አያጣውም…
እኛ ወደ ፊት እንሂድ!….ይሄ በሌላ ግጥሟ እንዲህ ነጥሮ ይወጣል።…..አዎ አንድም ‹ወደምትሄድበት ’ኹለትም ‘ወደምታስተካክለው’ የምትነጉድበት ነው። ከዚህ ጊዜ በኋላ ማልቀስ ይቀራል፤ ማኩረፍ ይቀራል፤ ማዘን ይቀራል፤ መብከንከን ይቀርና ሕይወት በመልኳ አንድም እንዳይደገም ጸራለች፤ ኹለትም ትምህርቷን ይዛ በሌላ አቅጣጫ ትቀጥላለች። ‹ከፍቅር ተማርኩ› ያለ ሰው ባይገጥመኝም ተምሬኣለሁ ብላናለች አበባ በግጥሟ።
‘አንዳንድ ቀን አለ… ረቡዕ የመሰለ’
በአበባ የግጥም ስብስብ ውስጥ ይህን የመሰሉ ወደ ዐራት ገደማ ግጥሞች አሉ። ‹ደ’ሞ አንድ ሰው አለ…ረቡዕ የመሰለ!›፤ ‹ደ’ሞ አንድ ሰው አለ… ሐሙስ የመሰለ!› ፤ ‹ደ’ሞ አንድ ሰው አለ… እሁድ የመሰለ!›፤ ‹ደ’ሞ አንድ ሰው አለ… ጥቅምት የመሰለ!› የሚሉ።
በተለይ ረቡዕ እና ጥቅምትን የታከኩት ኹለት ግጥሞች ልብን ያሞቃሉ፤ ሰውን ያከብራሉ። አሁን እናንተ ረቡዕ ላይ ናችሁ? አፋችሁ ከምን ይከለከላል? ምላሳችሁስ? መከልከል መፍቀድ ነው መፍቀድም መከልከል ነው። እናም ይህችን ፍልስፍና ከጥንት እስከ ዛሬ ብዙ ብዙ አላነጋገረችም? ረቡዕ ከማክሰኞ የወሰደውን ያህል ይዞ፤ ከራሱም ክልከላ ጨምሮ በከፊል የፈቀደውን ሰጥቶ አሸክሞ ለእሁድ ማቀበሉ ላይቀር፣ ረቡዕ ላይ አይሁድን አትሁኑ አልተባልንም?
ይሄንን ጉዳይ የሥነ ልቦና ባለሞያዎች ሲያብራሩት ደግሞ እንዲህ ይላሉ። ሰው ያላደረገውን በአንድም በሌላም መንገድ ማድረጉ አይቀርም፤ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ። የረቡዕ ልጆች እንዴት ናችሁ? ጾም አይገድላችሁም፣ ሐሙስ ስላለላችሁ። ይሄንንም ለማየት ረቡዕን እባካችሁ ረቡዕን ማለፍ እንዳትረሱ። ረቡዕ ላይ…ረቡዕ ላይ…ረቡዕ ላይ… ረቡዕ ላይ…ሐሙስ ረቡዕን መፍታቱ አይቀርምና አትቸንከሩ ነው የሚሉት/ ደስ የሚል ቋንቋ አይመስልም/። ግና እንዲህ እንዲህ በሉ፦
“….ፍችና ቅበላን ባንድ ላይ ምትደግስ፤
ተራማጅ ናት ነፍሴ
ረቡዕን ሸኝቻለሁ ብቅ በል ሐሙሴ”
ሐሙስ ላይ እንዳንቀር ‹ደ’ሞ አንድ ሰው አለ… እሁድ የመሰለ!› እያልን እሁድን አርፈንና ተኩራርተን ማለፍ አይከብደንም፤ እያለችን ነው።
‘እሳትና እራት’
ደራሲና ገጣሚ ነቢይ መኮንን አንዲት የትርጉም ግጥም አለችው፤ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የታተመች። እንዲህ ትላለች፦
“አንቺ የሳት እራት የእሳት ወዳጅ፤
ምናባቴ ላርግሽ
አንቺን ማቆም ባልችል እሳቱን ላጥፋ እንጂ”
/ቃል በቃል አይደለም/።
እሳትና እራት ይከብዳሉ። ማን በሳት ጥሮ ግሮ ለፍቶ ወጥቶ ወርዶ እራቱን አልበላም? ለልጅነታችሁ እንዴት ነበር እሳት፤ እሳቱና መብራቱ መብራቱና እራቱ፤ እራቱና ጥናቱ፤ ላምባውና ወጪው። ለወጣትነታችሁ እንዴት ነበር እሳት፤ እሳቱና መብራቱ መብራቱና እራቱ፤ እራቱና ጥናቱ፤ ላምባውና ወጪው/ ኤሌክትሪኩ ልበል/ በስተርጅናስ…?።
ይሄ የብዙ ኢትዮጵያውያን የሕይወት ተሞክሮ ነው። በአበባ ግጥም ውስጥ ግን ለእሷ/ ለአንዲት እናት፤ በጀርባዋ ለተሸከመችውና ለእድር እቁብ ማኅበርና ለእለት ወጪ የምታወጣውን የምታገኝበት ምናልባትም ብቸኛ የሕይወት መንገድና ሥራዋ ስለሆነው ስለ ማገዶ በጀርባ ተሸክሞ ሸጦ ስለማደር የጻፈችውና ሰውኛ ዘይቤ የተንጸባረቀበት ነው። በግጥሙ ውስጥ ደረቅ እንጨትነት ወይም ማገዶነት ከእናትነት ያበልጣል።፡ ይሄ ተፈጥሮን ይጋፋል። ችግርን ያገዝፋል።፡ ሕይወትን ያምታታል። ታላቁን የሰው ልጅ ፍሬ አልባ ያደርጋል። አመድ ሆኖ ተኖ አይቀርምና!።
ይህ በ21ኛው ዘመን በቅርቡ አንዲት እናት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዚህ መልኩ ያሳደገችው ልጅ ተመርቆ፤ ዩኒቨርሲቲው በር ፊት ለፊት እሱ እንጨቷን ተሸክሞ እሷ በአንጻሩ የልጇን ጋዎን ለብሳ አልታዘብንም? አበባም መጀመሪያ ቅጠል፤ ከዚያም ዛፍ ለጥቆም እንጨት ለሆነና ማገዶ እንዲሆን እሷ ተሸክማው የምታወጋውን ግጥም እጅግ በሚመስጥ ሰውኛ በሆነ፤ ልብን በሚሸረክት፤ ዘመንን በሚያስርድ፤ ልምድን በሚሞርድ መንገድ ገልጻዋለች። እስቲ ደግማችሁ ደጋግማችሁ አንብቡት!
አበባ ከምርጥ ገጣሚነቷ ባሻገር አዳዲስ ነገሮችንም ይዛ መጥታለች። እነዚህም ለምሳሌ፦ ቅርንጫፋም ግጥም፤ ባሌ ሌባ ወይም ሌባ ባሌ፤ የመጨረሻው ገጽ፤ አለ ማለት ነው?
አበባን የማውቃት ከዐስርት ዓመታት በፊት ነው። የደቡብ ዩኒቨርሲቲ የመቅረዝ የሥነ ጽሑፍ በረከት ሆና። ያ ዘመን ደግሞ ዘመነኞቹን ያገናኘ ጉደኛ ጊዜ ነበር። እኔ እንኳ በግሌ የምወድላት ከድሮ ግጥሞቿና እዚህ ከተካተቱት ውስጥ ፦
“ታየኛለች ብለህ ታማኛለህ አሉ፤
ታየዋለች ብሎ ያወራል ሰው ሁሉ፤
ደግሞ እኔም አልክድም ማየቴ እርግጥ ነው፤
ግና ልጠይቅህ….
እንዳየሁ ስታይ አንተስ ጨፍነህ ነው?” የሚለውን ነው።
በመጨረሻም በሌላ አንድ ግጥሟ ልሰናበታችሁ፦
በየደረስክበት በያለፍከው መንደር፤
እረስቻታለሁ ብለህ የምትናገር፤
ውሸትህን እንጂ ለምዶብህ መግደርደር
ብትረሳማ ኖሮ….
እንደረሳኸኝም አታስታውስ ነበር” /ገ.53/
አበባ “የመጀመርያዎቹ መጨረሻ፤ የመጨረሻዎቹ መጀመርያ ነንና እናምራለን” እንዳላልን ለምን ግን የመጽሐፉን ገጽ 102 አደረግሽው? ውባለም ምስጋና ይድረስልኝ! ሠላም!
የጽሑፉን አዘጋጅ በድሉ አበበን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይችላሉ።
ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015



