ለበርካታ ዓመታት አወዛጋቢ ሆኖ የቆየው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የኦሮሚያ ክልል የወሰን ጉዳይ፣ ከወራት በፊት ድንገት መካለሉን መንግሥት ማሳወቁ የሚታወስ ነው። የወሰን ማካለሉ ድንገት የተሰማ ከመሆኑ በላይ ያልተጠበቁ በርካታ አካባቢዎችን ወደ ኦሮሚያ ክልል በማካተቱ በተለይ ከአዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ በተካለሉ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ይገልጻሉ። በድንገት ሳናውቅና ሳንወያይበት ወደ ኦሮሚያ ክልል ተካለናል ከሚሉት ሰዎች መካከል በኮዬ ፈጬ ኮንዶሚንየም ነዋሪ የሆኑት ሻምበል ታረቀኝ አዝዜ ስለ ጉዳዩ ሐሳባቸውን እንደሚከተለው ከትበዋል።
የኮዬ ፈጬ ኮንዶሚንየም ቤት፣ 10/90 በቅድሚያ 2009 በደሃ ደሃ ተብሎ፣ 10/90 የቤት ልማት 9400 አባወራ ሲሰፍር ለኹለት ዓመት ያለምንም ውሃና መብራት ተሰቃይቶ የቆየ ሕዝብ ነው። ከዛ በመቀጠል ለመምህራን በቤት ኪራይ ተጨማሪ ተሰጠ። በ20/80 በእጣ ቤት የደረሳቸው ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ ከልደታ፣ ከፒያሳ፣ ከቂርቆስ እስከ ቡልጋሪያ በልማት ተነሽ ተብሎ የሰረፈበት ኮንዶሚንየም መሆኑ ይታወቃል። ከልማት ተነሺዎች በተጨማሪ፣ የገበሬ ልማት ተነሺዎችም የኮንዶሚንየም ቤት ተጠቃሚ ናቸው።
አጠቃላይ የኮዬ ፈጬ የኮንዶሚንየም ቤት ብዛት 55 ሺሕ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወደዚህ አምጥቶ ከጣለ በኋላ ምንም ነገር፣ አንድም አባል ባልተወያየበት እና ባልተስማማበት መሠረት ወደ ኦሮሚያ ክልል ተካላችኋል ተብሎ ተነገረ። የገበያ ከብት እንኳን ተደራድሮ ተስማምቶ ነው የሚሸጠው። የሰው ልጅን በእንደዚህ ዓይነት አስከፊ ሁኔታ 82 ብሔር ብሔረሰብ የሚኖርበት ኮንዶሚንየም በአንድ ቋንቋ ትተዳደራለህ ብሎ ማሰብ አንዱ የመንግሥት አካል ቀርቶ ሕፃን ልጅ የማያስበው አስተሳሰብ ነው።
በኮዬ ሕዝብ ላይ በዶክተር ዐቢይ መንግሥት አስተዳደር የተደረገውን ግፍና በደል የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር ይመልከትልን። እውነት ተዳፍና አትቀርም፣ አንድ ቀን ብርሃን ትበራለች። ለደካማ እናቶችና ሕፃናት አረጋዊያን ሀዘን ምክንያት የሆነውን መሬት ላይ የታየውን እውነታ የዓለም ማኅበረሰብ ይመልከትልን።
የኮየ ፈጬ ነዋሪ መብራት እንዲያገኝ ተፅእኖ በመፍጠር ለ6 ዓመት ተሟግቻለሁ። በ6/12/2014 ኮዬ ወደ ኦሮሚያ ተካሏል በማለት በወረዳ 09 ጽሕፈት ቤት የተዘጋጀ ስብሰባ እንዳለ ተነገረኝ። ቦታው ስገኝ በስብሰባው ላይ ሞባይል ይዞ መግባት አይቻልም ነበር። ስብሰባውንም የሚመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑትና የድንበር ኮሚሽን የተባሉት ዘላለም ሙላቱ እና የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ ሀቢባ ሲራጅ እና የወረዳ 09 ሥራ አስኪያጅ መኪያ ሁሴን ሸካ ነበሩ።
በዚህ ስብሰባ ላይ ተገኝቼ ሐሳብ ሲንሸራሸር ቀጥታ ወደ ኦሮሚያ መጽደቁን ተቀበሉ እና ሕዝብ አሳምኑ የሚል ግዴለሽነት ወይም አስገዳጅ ትዕዛዝን ነበር የሰማሁት።
በስብሰባው ላይ የመናገር እድል ካገኘሁ በኋላ፣ በተለያዩ ሁኔታ ከመሐል አዲስ አበባ ተነስቶ ኮዬ የሰፈረን ሕዝብ በድንገት ወደ ኦሮሚያ ክልል ተካለሀል የሚለውን ሐሳብ ተቃወምኩ። ወያኔ የደሃ ደሃ ብሎ የኮንዶሚንየም ነዋሪዎችን አምጥቶ ወረወረን። ተረኛውስ ለኮንዶሚንየም ሕዝብ ምን አስቦ ነው? ስለዚህ ወደመጣንበት ቦታ ከተማ አስተዳደሩ ሊመልስልን ይገባል የሚል ቅሬታ አቀረብኩ። ቅሬታዬን በማማረር ከማቅረቤ ባሻገር፣ ያለው የሕዝብን ችግር ለማቅረብም ሆነ ለመሞገት ወደኋላ አልልም።
ወያኔ አንገቴን ቆርጦኝ ከሆነ እናንተ ደግሞ እግሬን እስከምትቆርጡኝ ከመናገር አልቆጠብም በሚል ምሬቴን አቅርቤያለሁ። ይሁን እንጂ ያለሕዝብ ፍላጎት ያለውይይት የሕዝቡ ዶክመንት ወደ ኦሮሚያ ተላልፎ ሲሰጥ ሕገ መንግሥት የጣሰ፣ ሕግን የተፃረረ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ሳይጸድቅ ተወሰነ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመረጡት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሆኖ ሳለ የሕዝብን አደራ በመርሳት የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ የሚረዱ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተመረጡ መሆናቸውን ረስተው፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ ግን እሳቸው ወደ ሥልጣን ሲመጡ ለውጥ መጣ ብሎ በደስታ የተቀበለ ነበር። ኮዬ ፈጬ ወደ ኦሮሚያ መከለል ሕዝብን ሳያወያዩ ለአንድ ክልል ያደሉ ይመስላል። አንድ ብሔር ወይም ወገንተኝነት የታየበት አስነዋሪ ተግባርን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲፈጸሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ከዚህ በፊትም ተደርጎ የማይታወቅ ነው።
ከዚህም በኋላ የማይደረግ ነው። የታሪክ ተወቃሽ ያደርጋል እንጂ፣ ሕዝብን ያላማከለ ሥራ ሁሉ ለጊዜው የተሳካ ሊመስል ይችላል። ከጊዜ በኋላም ቢሆን ለታሪክ አሳፋሪ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ። ወገንተኝነት የተንጸባረቀበት ውሳኔ የጊዜ ጉዳይ እንጂ በዘላቂነት መፍትሔ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም።
በአዲስ ማለዳ ጋዜጣ የሚወጣን ይሄን ሐሳቤን አንብባችሁ ችግሩን ብታዩት የተሻለ ይሆናል። ይህ ሐሳብ የግለሰብ አይደለም፣ 55 ሺሕ አባወራ በአጭሩ በአማካይ በአምስት ቤተሰብ ቢባዛ 275 ሺሕ ሕዝብ ሐዘንና ምሬት መሬት ላይ ጠብ እንደማይል ማሰብ ጥሩ ነው።
ያለ ሕዝብ ፍላጎትና ውይይት ድንገት ወደ ኦሮሚያ ክልል ተካላችኋል የተባለው ውሳኔ ቢጸና እንኳን፣ ቢያንስ እንኳን በጉልበት ተቀበሉና ተቀመጡ ከተባልን መብታችን ተጠብቆ በቋንቋችን 82 ብሔር ብሔረሰብ በቋንቋቸው በባህላቸው እንዲያወሩ እና የእያንዳንዱ አባል ሠነድ በነበረበት በልዩ ዞን የሚተዳደር እንዲሆን እንጠይቃለን።
ወደ ኦሮሚያ ክልል ተካለሀል የተባለው አዲስ አበባ ነዋሪ ኹሉንም ብሔር ብሔረሰቦች ያካተተ የአዲስ አበባ ሕዝብ ነው። ይህን ሕዝብ ወደ ኦሮሚያ ክልል ከመጨፍለቅ በቋንቋው የሚገለገልበት ሥርዓት ለመፍጠር የልዩ ዞን አስተዳደር ለሲጠው ይገባል የሚል ምክረ ሐሳቤን የሚመለከተው አካል በአንክሮት ይመልከተው።
ገና ከአሁኑ የሚታዩ ሥርዓት አልበኝነቶች፣ የኮዬን ሕዝብ ነጻነትና የሰብዓዊ መብት የሚጥሱ መሆናቸውም ልብ ሊባል ይገባል። እኛ የኮዬ ነዋሪዎች ያለፈቃዳችን በሕዝብ ሥም ተዋሽቶ “ሕዝብ ተወያይቶ የተወሰነው ነው” የተባለውን የወሰን ማካለል ጉዳይ ለውይይት ቀርቦ ተወያይተን የተስማማንበት አለመሆኑ በግለጽ ይታወቅልን።
የኮዬን ሕዝብ አዳነች አቤቤ ሸጣናለች። አብዛኛው የኮዬ ኮንዶሚንየም ነዋሪ በተለያየ ሁኔታ ከመሐል አዲስ አበባ የመጣ ሲሆን፣ የተወሰኑ በኮንዶሚኒየም ቤት ልማት የተነሱ አርሶ አደሮች የሚኖሩበት አካባቢ ነው። ይህ ሆኖ ሳለ ድንገት ወደ ኦሮሚያ ክልል መካለላችን፣ ከአሁኑ የሚታዩ ምልክቶች ጤነኛ አለመሆናቸውም ልብ ሊባል ይገባል። ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚመጡ ሰዎች ሰው የሌለባቸው ኮንዶሚንዬም ቤቶችን ሰብረው በመግባት አንወጣም ማለት መጀመራቸው ሕዝቡን ለስጋት ዳርጓል።
ባዶ ቤት ሰብረው በመግባት አንወጣም ማለት ከጀመሩት አካላት መካከል የመንግሥት የጸጥታ አካላት ጭምር የሚገኙበት መሆኑ ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል። በወራት ልዩነት የሚታዩት ችግሮች፣ ወደፊት ምን ሊያጋጥም እንደሚችል ስጋት የሚጭሩ ናቸውና መንግሥት የኮዬን ሕዝብ ችግር ተመልክቶ በነጻነት የምንኖርበት ሁኔታ ከላይ እንደገለጽኩት አማራጮችን እንዲፈልግ እናሳስባለን።
ቅሬታችንን በቅደም ተከተል አቤቱታ እየጠየቅን እንደሆነ ይሰመርበት። ከዚህ በመቀጠል የቱሉ ዲምቱ፣ ፉሪ፣ ጋርመንት፣ ጀሞ ኮንዶሚንየም አጠቃላይ የተጠቀሱ ቤቶች የተሠራበት ቦታ ግምትና የግንባታ ወጪ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ንብረት ሆኖ ሳለ ወደ ኦሮሚያ ክልል ሲከለል ምንም ግምት ሳይጠየቅ በነጻ ተላልፏል። ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትዝብት፣ ለምሁራን እና ጋዜጠኞች የቤት ሥራ አጠቃላይ ለማኅበረሰብ የተሰጠ የቤት ሥራ ሆኖ ይነበብ።
ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015



