ዕረቡ ጥቅምት 16 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በምስላዊ የጥበብ ሥራዎቹ የሚታወቀው ኢትዮጵያዊው አርቲስት ፋኑኤል ልዑል፣ በምርጥ 30 የአፍሪካ “ኪፕ ዎኪንግ” (Keep Walking: Africa Top 30 List) ውስጥ እንዲካተት መመረጡ ተገለጸ።
አርቲስት ፋኑኤል፣ ጆኒ ዎከር (Johnnie Walker) እና ትሬስ ቲቪ (Trace TV)፤ በአፍሪካ የሚገኙና ባህላቸውን በሙዚቃ፣ በፊልም፣ በሚዲያ፣ በፋሽን እና በጥበብ ወደፊት የሚገፉ አፍሪካውያን ፈጣሪዎች እና ባለራዕዮችን ለመለየት ባዘጋጁት ውድድር ላይ ነው ምርጥ 30ዎቹ ውስጥ መካተቱ የተገለጸው።
ይህንንም በማስመልከት ትናንት ጥቅምት 15፣ 2015 በአዲስ አበባ ሀያት ሪጀንሲ ሆቴል የእውቅና መርሃ ግብር ተከናውኗል፡፡ በመርሃ ግብሩ ላይም በአህጉሪቱ ካሉ ከፍተኛ ተሰጥኦ ካላቸው ሰዎች ጋር የሚሰሩ ማናጀሮችና የኢንዱስትሪ መሪዎች ለኹለት ወራት ባደረጉት ጥናት እና ፍለጋ መሠረት የምርጥ 30ዎቹ ዝርዝር ይፉ መደረጉ ተገልጿል።
በዝርዝሩ ውስጥም ከአንጎላ፣ ኮትዲቯር፣ ካሜሩን፣ ኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ሞዛምቢክ፣ ናይጄሪያ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያ እና ዛምቢያ የተውጣጡ የምርጥ አፍሪካዊ “ኪፕ ዎኪንግ” አርቲስቶች እና የፈጠራ ባለሞያዎች መካተታቸው ተነግሯል።
የምስላዊ አርቲስቱ ፋኑኤል ልዑል በዚህ ምርጥ 30 የአፍሪካ “ኪፕ ዎኪንግ” ዝርዝር ውስጥ የተካተተ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ታዋቂ የአፍሪካ ሙዚቃ ፕሮዲዩሰሮች፣ የፋሽን ባለሙያዎች፣ የፊልም አዘጋጆች፣ የምስላዊ ጥበብ ባለሙያዎች እንዲሁም የሚዲያና ማስታወቂያ ባለሙያዎችም በዝርዝሩ መካተታቸው ተገልጿል።

ፋኑኤል የአህጉሪቱን ታላቅ ታሪክ የሚተርክ እና የኢትዮጵያ አርበኞችን እንደ ልዕለ ጀግኖች የሚያቀርብ ‘ቀዳማዊ’ የስዕል መጽሔት ፈጣሪና፤ በተለያዩ የሙዚቃ ሥራዎች ላይ የዲጂታል ጥበብን በመጠቀም ምስላዊ የጥበብ ሥራዎችን በመስራት የሚታወቅ ወጣት ባለሙያ ነው።
በቅርቡም በዱባይ ከምትኖረው ኢትዮጽያዊ የፋሽን ዲዛይነር ፌይሩዛ ሙደሲር ጋር ትብብር በማድረግ፤ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የዲዛይነሯን የፋሽን ሥራዎች ከዲጂታል አርት ጋር ያቀላቅላል የተባለለትን ሥራ የሠራ ሲሆን፤ ብዛት ያላቸውን የሮቦት አፍሪካዊ ማስኮችም ለሽያጭ ቀርበውለታል።



