ኢትዮ ቴሌኮም “ቴሌ ክላውድ” የተሰኘ የክላውድ አገልግሎት አስጀመረ

0
1024

ሐሙስ ጥቅምት 17 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞቹን የዕለት ተዕለት የቢዝነስ እንቅስቃሴ ለማዘመን እና ለማሳለጥ ያስችላል ያለውን “ቴሌ ክላውድ” የተሰኘ የክላውድ አገልግሎት ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 17/2015 በሳይንስ ሙዚየም በይፋ አስጀምሯል።

ኢትዮ ቴሌኮም በአገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የግልና የመንግስት ተቋማት ከፍተኛ የመረጃ ክምችት እና አጠቃቀም እንዲሁም ተዛማች የክላውድ አገልግሎት ፍላጎት መሠረት በማድረግ ለደንበኞቹ አገልግሎቱ ማስጀመሩን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ተናግረዋል።

አዲሱ የክላውድ አገልግሎት አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ፤ አገልግሎቱ ተቋማት የራሳቸውን የመረጃ ማዕከል መገንባት ሳያስፈልጋቸው ካሉበት ሆነው የፈለጉትን መረጃ ከኢትዮ ቴሌኮም ማግኘት የሚችሉበት አሰራር መሆኑን አብራርተዋል።ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ አክለውም የክላውድ አገልግሎቶቹ በሦስት አማራጮች መቅረባቸውንም ገልጸዋል።

እነርሱም አንደኛው (Infrastructure as a Service (laaS) ሲሆን፤ ተጠቃሚዎች እንደ አስፈላጊነቱ ካሉበት ሆነው የግል መረጃዎቻቸውን ማስቀመጥ፣ መቀመር፣ ለደንበኞቻቸው የተለያዩ አገልግሎችን መስጠት የሚያስችል የክላውድ አገልግሎት መሆኑን አስረድተዋል።

ኹለተኛው ደግሞ (Platform as a Service (PaaS)-) ሲሆን፤ በዋነኛነት የሶፍትዌር አልሚዎች ካሉበት ሆነው ላበለፀጓቸው ሶፍትዌሮች የተሟላ የዳታቤዝ ማኔጅመንት ሲስተም (MySQL DB) መጠቀም ያስችላቸዋል የተባለ ሲሆን፤ አልሚዎች ሶፍትዌሮቻቸውን ማስቀመጥ፣ መጠቀም እንዲሁም ለሌሎች መሸጥ እንዲችሉ ያደርጋል ብለዋል።

ሦስተኛው አማራጭ ደግሞ (Software as a Service (SaaS)-) ሲሆን፤ ደንበኞች የተለያዩ በውጭ ምንዛሪ የላይሰንስ ክፍያ በመክፈል ያገኟቸው የነበሩ ሶፍትዌሮችን ከቴሌክላውድ በተመጣጣኝ ክፍያ በብር ማግኘት የሚችሉበት አገልግሎት መሆኑን ገልጸዋል።በዚህም የ(Software as a Service (SaaS)-) አማራጭ ላይ ኢትዮ ቴሌኮም ለመነሻነት ሦስት አገልግሎቶችን ማቅረቡን የገለጹት ፍሬህይወት፤ በቀጣይ የተለያዩ ተጨማሪ ሶፍትዌሮች በክላውዱ እንደሚካተቱ ተናግረዋል።

ከነዚህም አማራጮች ውስጥ አንደኛው (Oneoffice productivity and collaboration solution) ሲሆን፤ በአገልግሎቱ ደንበኞች በቢሮዎቻችው የጽሁፍና ሌሎች የቢሮ አገልግሎቶች የሚያከናውኑበት የኦፊስ መተግበሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላኛው (Video Management System (MS) ሲሆን፤ ደንበኞች ይህን አገልግሎት በመጠቀም የደህንነት የቪዲዮ ካሜራዎቻቸውን በማገናኘት የቪዲዮ ማስተዳደሪያ ሲስተም እና የሚፈልጉትን ያህል የዳታ ቋት ማግኘት የሚችሉበት ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ሦስተኛው የ(SaaS) አማራጭ (Smart Education productivity /Uleaming) ሲሆን፤ የትምህርት ተቋማት በስማርት ትምህርት በመታገዝ የርቀት እና የገጽ-ለገጽ ትምህርትን በቪዲዮ ጭምር በመታገዝ በዘመናዊ መልኩ በመስጠት ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን የሚያገኙበት መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም ለተማሪዎቻቸው የተሟላ ቤተ-ሙከራ፣ ማስታወሻ አያያዝ የትምሕርት ግብአቶችን ማጋራት፣ የትምህርት መርጃ እና ምዘና ማካሄድ ይችላሉ ብለዋል።

ድርጅቶች እና ተቋማት የቴሌክላውድ አገልግሎትን በመጠቀም ለቴክኖሎጂ መረጣ፣ ለመሠረተ ልማት ግንባታ፣ ሠልጠና እና ጥገና የሚወስደውን ጊዜ እንዲሁም የውጪ ምንዛሪ ክፍያ በማስቀረት፤ የቢዝነስ እንቅስቃሴያቸው እና የአገልግሎት ጥራትን በማሳደግ ላይ ብቻ እንዲየያተኩሩ በማድረግ ተወዳዳሪነታቸው እና ምርታማነታቸው እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል።

ይህንንም የክላውድ አገልግሎት ለመጠቀም የሚሹ ደንበኞቸሰ በኢትዮ ቴሌኮም ድህረ ገጻ cloud.ethotelecomet ተጠቅመው አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉና ክፍያቸውንም በቴሌብር በኩል ባሉበት መክፈል እንደሚችሉ ተነግሯል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here