በደቡብ ክልል ጎፋ ዞን መሎ ጋዳ ወረዳ በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ምክንያት ከሥራ ከተባረሩ 119 ሠራተኞች መሀል ትክክለኛ ማስረጃ ያላቸው ሠራተኞች መገኘታቸውን ወረዳው አስታወቀ።
የመሎ ጋዳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ፍቅሬ አበበ ለአዲስ ማለዳ እንዳታስወቁት፣ በቁጥር ያልተገለጹ የማባረር እርምጃ የተወሰደባቸውና ባቀረቡት ቅሬታ መሠረት ማስረጃቸው በድጋሚ ሲታይ ትክክል ሆኖ የተገኘ ሠራተኞች ወደ ሥራ እንዲመለሱ እንደተደረገ ተናግረዋል።
በወረዳው ተቀጥረው በሚሠሩ 208 ሠራተኞች ላይ ከዞንና ከወረዳ በተውጣጣ የባለሙያዎች ኮሚቴ በተደረገ ማጣራት 119 ሠራተኞች ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ተገኝቶባቸዋል በሚል ሰኔ 27/2014 በተጻፈ ደብዳቤ ከሥራ የማባረር እርምጃ ተወስዶባቸዋል።
ይሁንና ከሥራ ከተባረሩት ሠራተኞች መካከል ትክክለኛ የትምህርት ማስረጃ ያላቸው ሠራተኞች ቅሬታቸውን በተደጋጋሚ እያቀረቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ለቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ያቀረቡት ቅሬታ ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ሥራ የተመለሱ ሠራተኞች እንዳሉ ፍቅሬ አረጋግጠዋል።
ማስረጃዎችን የማጣራት ሂደቱ ምን ያህል አስተማማኝ ነበር ተብለው የተጠየቁት ፍቅሬ፣ በኮሚቴው ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ የብቃት ማረጋገጫ ምዘናዎችን ሳይቀር ለማረጋገጥ እንደተሞከረ ገልጸዋል። አያይዘውም በኮሚቴው መረጃዎችን የማጣራት ሥራ ላይ ክፍተት እንደነበረ በቅሬታዎች ምክንያት ማስረጃዎች ሲጣሩ መረጋገጡን ጠቅሰዋል።
ይሁንና፣ ይህ የተፈጠረው ሆን ተብሎ ሳይሆን መረጃዎችን ለማጣራት ውስብስብ የሆኑ መንገዶችን መጠቀም አሰፈላጊ ስለነበር ነው ብለዋል። እንደ ምሳሌም ሐሰተኛና እውነተኛ ማስረጃዎችን አደባልቀው የያዙ ሠራተኞች እንዳሉ ገልጸው፣ እርምጃ ከመወሰዱ በፊት የተቻለውን ያህል ማጣራት ለማድረግ እንደተሞከረ ተናግረዋል።
አሁንም ያለ አግባብ ከሥራ ተባረናል የሚሉ የወረዳው ሠራተኞች ያሉ ሲሆን፣ ቅሬታቸው ላለፉት ሦስት ወራት ምንም ዓይነት መልስ እንዳላገኘ ተናግረዋል።
በ2011 የጋሞ ጎፋ ዞን ጋሞ እና ጎፋ በሚባሉ ኹለት ዞኖች ሲከፈል ይሠሩበት ከነበረው መሎ ኮዛ ወረዳ ወደ መሌ ጋዳ ወረዳ እንደተዘዋወሩ የገለጹ አስመላሽ መንገሻ የሚባሉ ቅሬታ አቅራቢ እንደሚሉት፣ በአጠቃላይ ለአምስት ዓመት ከ10 ወር ከሠሩበት ሥራቸው ያለ አግባብ እንደተሰናበቱ ተናግረዋል። ሻሸመኔ በሚገኘው ፓራዳይዝ ኮሌጅ በግል የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአካውንቲንግ እንዳገኙ የገለጹት አስመላሽ፣ በመሎ ጋዳ ወረዳ ፋይናንስ ቢሮ የኦዲትና ኢንስፔክሽን ሥራ ሂደት የቡድን መሪ ሆነው ሲያገለግሉ እንደነበር ተናግረዋል።
ይሁንና በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንድሰጥ ሳልጠየቅ ሰኔ 27/2014 ደብዳቤ ደርሶኛል የሚሉት አስመላሽ፣ የትምህርት ማስረጃቸው ትክክል እንደሆነ በማስረዳት ቅሬታ ባቀርብም እስካሁን ምንም ዓይነት ምላሽ አልተሰጠኝም ብለዋል። ከሥራ ሲባረሩም የሠሩበት የሰኔ ወር ደሞዝ እንዳልተሰጣቸው ገልጸው፣ ትክክለኛ ምላሽ ባለማግኘታቸው ለችግር እንደተጋለጡ ተናግረዋል።
ሌላው ቅሬታ አቅራቢ ገብረአብ አያሌው እንደሚሉት ደግሞ፣ ከሳውላ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በሰርቬይንግ በደረጃ 4 የተመረቁና የብቃት ማረጋገጫ ያላቸው ሲሆን፣ በወረዳው ማዘጋጃ ቤት በባለሙያነት ተቀጥረው ይሠሩ ነበር። ይሁንና ደሞዛቸው ተቀንሶ በተመሳሳይ የሥራ መደብ ይሠራ ከነበረና በሥራ ልምድ ከሚያንሳቸው ሰው በደሞዝ እንዲያንሱ እንደተደረጉ ተናግረዋል። በዚህ ጉዳይ ቅሬታቸውን በማቅረብ ላይ እንዳሉም ከሌሎች ሠራተኞች ጋር በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በሚል ምክንያት ከሥራ እንደተባረሩ ገልጸዋል።
ቅሬታ አቅርበው ስላልተመለሰላቸው ቅሬታ አቅራቢዎች የተናገሩት ፍቅሬ፣ የማጣራት ሂደቱ ጊዜ ስለሚወስድ እንጂ የኹሉም ቅሬታ ምላሽ ያገኛል ብለዋል። ቅሬታ አቅራቢዎች ስላልተከፈላቸው ደሞዝም የተጠየቁት ፍቅሬ፣ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ይዘው የተገኙትን ሠራተኞች ‹‹እንኳን ደሞዝ ልንከፍላቸው ከሥራ እስኪሰናበቱ ድረስ የወሰዱትን ደሞዝ ለማስመለስና አስፈላጊው ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለማድረግ እየተዘጋጀን ነው።›› ሲሉ ተናግረዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015



