ሸገር ብዙኀን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት እና ሠራተኞቹ በጥቅማጥቅም ተካሰሱ

0
1546

የሸገር ብዙኀን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ሠራተኞች የጥቅማ ጥቅም መብታችን አልተከበረም በሚል ድርጀቱ ላይ ክስ መሥርተው በፍርድ ቤት ክርክር ላይ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

በተቋሙ መመሪያ መሠረት የድርጅቱ ዓመታዊ አፈጻጸም በተለይ ከ90 በመቶ በላይ ከሆነ፣ ለሠራተኞች የሥራ እርከን ጭማሪ እንዲሁም የገንዘብ ጉርሻ (bonus) የሚያገኙ ቢሆንም፣ አፈጻጸሙ ከ90 በመቶ በላይ በሆነባቸው ባለፉት ተከታታይ ኹለት ዓመታት ይህ ሳይፈጸም ቀርቷል ነው ያሉት።

ይህን ተከትሎም የድርጅቱ የሠራተኞች ማኅበር ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ክስ መመሥረቱንና ፍርድ ቤቱም ለሠራተኞች ወስኖ የነበረ መሆኑን ገልጸዋል። ሆኖም ውሳኔውን ተከትሎ ተቋሙ በሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ማለቱ ተሰምቷል።

ይህም በመጭው ኅዳር ወር የፍርድ ቤት ቀጠሮ የተያዘለት ሲሆን፣ የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ ግን ሠራተኞች ክሱን የሚያቋርጡ ከሆነ በተለይ ለአዲስ አበባ መንግሥት ሠራተኞች ተግባራዊ የተደረገውን የቤት ኪራይ ድጎማ አበልና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን እንዲያገኙ እንደሚያደርግ እንደገለጹላቸው ሠራተኞቹ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሆኖም ያለምንም መተማመኛ የሥራ አስኪያጁን ቃል ተቀብለው ክሱን እንደማያቋርጡ በመጥቀስ፣ ጥያቄ ስናነሳ ለኹሉም ነገር የአገሪቱን ሁኔታ እየጠቀሱ ሠራተኛው እየተበደለ ነው ብለዋል።

በድርጅቱ የትራንስፖርት ትኬት ቆራጭ ነኝ ያሉና ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሠራተኛ፣ <<በመመሪያው መሠረት አፈጻጸማችን ከ90 በመቶ በላይ ሆኖ፣ በአዲስ አበባ ካሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አንደኛ ብንሆንም፣ ቦርዱ አላጸደቀም በማለት የምናገኘው ጥቅማ ጥቅም ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም>> ብለዋል።

ለሦስት ዓመት ያህል ካለው ኑሮ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም ደሞዝ ነው የሚከፈለን የሚሉት ሠራተኛው፣ ወርሃዊ ደሞዜ 2 ሺሕ 500 ብር ነው ሲሉ ተናግረዋል። የጽዳትና የመኪና ዕጥበት የሚሠሩ ሠራተኞችም ከዚህ ያነሰ ዝቅተኛ ክፍያ እንደሚከፈላቸው ነው የገለጹት።

ሌላኛው ሠራተኛ በፊት በየሦስት ወሩ ሲሰጡ የነበሩ እንደ ሶፍትና ሳሙና ያሉ ጥቅማ ጥቅሞች ከቆሙ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል ብለዋል። ስለሆነም፣ ሠራተኛው የደሞዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄው ስላልተመለሰለት በመማረሩ ማኅበረሰቡን በተገቢው ሁኔታ ማገልገል አልቻለም ሲሉ ተደምጠዋል። እንዲሁም ያለበቂ መለዋወጫና ያለበቂ መኪና ነው እየሠራን ያለውም በማለት አክለዋል።

የሸገር ብዙኀን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሳሙኤል ፍስኃ ከሠራተኞች የተነሱትን ቅሬታዎች አስመልክቶ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ማብራሪያ፣ ከአንድ ዓመት በፊት የሠራተኛ ማኅበሩ በተቋሙ ላይ የመሠረተው ክስ በሂደት ላይ መሆኑን ጠቅሰው የመጨረሻውን ውሳኔ እየጠበቅን ነው ብለዋል።

ተቋሙ የሚተዳደረው በቦርድ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፣ የሚያገኘውን የአፈጻጸም ውጤት ለቦርዱ አቅርቦ፣ ቦርዱ ካጸደቀ በኋላ በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት ነው የሠራተኞች ጥቅማጥቅም ተግባራዊ የሚደረገውም ሲሉ ተደምጠዋል።

ስለሆነም፤ ቦርዱ ምላሽ ባለመስጠቱና በመመሪያ መሠረት መሄድ ባለመቻሉ ሠራተኞች ጥቅማ ጥቅም ይገባናል የሚል ክስ መመሥረታቸውን ነው የገለጹት። ተቋሙ አልከፍልም የሚል አሠራር የለውም ያሉት ኃላፊው፣ ቦርዱ ለምን ምላሽ እንዳልሰጠ መመለስ ያለበት ቦርዱ እንጂ ተቋሙ አይደለም ብለዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here