የሰሊጥ ሽያጭ በኩንታል እስከ 2,000 ብር መቀነሱ ተገለጸ

0
2089

የሰሊጥ ገበያ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በኩንታል እስከ 2,000 ብር ድረስ መቀነሱን አምራች አርሶ አደሮች ገለጹ።

በአማራ ክልል ወልቃይት፣ መተማ፣ ሁመራ አርማጭሆ እና ቋራ አካባቢዎች ሰሊጥ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች እንደተናገሩት፣ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሰሊጥ እየተገበያዬ ያለው በኩንታል ከ8,000 እስከ 8,400 ብር ነው። ባለፈው ዓመት አንድ ኩንታል ሰሊጥ እስከ 10 ሺሕ ብር ይሸጥ እንደነበር ጠቅሰው፣ የዘንድሮው መሸጫ ዋጋ ግን የተመረተበትን ወጭ እንኳን እንደማይሸፍን ገልጸዋል።

በዘንድሮው ዓመት ለምርት ከፍተኛ ወጭ አውጥተናል ያሉት አርሶ አደሮቹ፣ የጉልበት ሠራተኛ ዋጋ ከባለፈው ዓመት አንጻር ከሶስት እጥፍ በላይ ጨምሯል፣ የሚታረሰውም በትራክተር በመሆኑ ለዚህ የምናወጣው ወጪ አምስት እጥፍ ነው የጨመረው ሲሉ ተደምጠዋል።

በዚህም 200 ሄክታር መሬት ያለው ገበሬ ለእርሻ 800 ሺሕ ብር አውጥቶ ለመሬት ጽዳት፣ ለአረም እና ለአጫዳ እንዲሁ ከፍተኛ ወጭ ማውጣቱ ከዋጋ መቀነሱ ጋር ተዳምሮ በአርሶ አደሩ ገቢ ላይ ተጽዖኖ መፍጠሩ ተነግሯል። ዋጋው በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተተመነ በመሆኑ እንዲስተካከል ቅሬታችን እስከ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት እናቀርባለን ብለዋል።

አርሶ አደሮች አክለውም፣ ‹‹በእኛ እምነት ሰሊጥ ከእኛ ገዝተው ወደ ውጭ ገበያ የሚልኩ ነጋዴዎች ዋጋው እንዲቀንስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ላይ ጫና አድርገዋል›› ነው ያሉት። መንግሥት ላኪዎች አገር ውስጥ የሚገዙበት ዋጋ ውጭ ገበያ ላይ ከሚሸጡበት ዋጋ እንዳይበልጥ መከልከሉን ተከትሎ ኪሳራውን እኛ ላይ እየጫኑት ነው በማለትም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ግብይቱ የሚከናወነው አቅርቦትና ፍላጎትን መሰረት አድርጎ በፍላጎት ነው ብሏል። የአገር ውስጥ የምርት ዋጋ ዓለም ላይ ባለው ዋጋ ይወሰናል ያለው ተቋሙ፣ ሆኖም በምርት ገበያው የሚከናወነው ግብይት ዋጋው ዓለም አቀፍ ገበያው ላይ ካለው ዋጋ እንዳይበልጥና አገራችንንም እንዳትከስር የመገበያያ ዋጋ በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በኩል በየሳምንቱ ይላክልኛል ነው ያለው።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ነፃነት ተስፋዬ፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሻጭና ገዥ በፍላጎት ላይ የተመሰረት ግብይት የሚፈጽሙበት መድረክ እንጂ ዋጋ የመወሰን ስልጣን የለውም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ፣ ላኪዎች በውጭ ገበያ ላይ ከሚሸጡበት በበለጠ አገር ውስጥ ሲገበያዩ አገሪቱ ኪሳራ የሚያጋጥማት በመሆኑና ይህን ለመከላከል ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ዓለም አቀፍ ገበያውን መሠረት በማድረግ ሳምንታዊ የዋጋ ጣሪያ አዘጋጅቶ እንደሚልክ ነው ነጻነት የጠቆሙት።

ሳምንታዊ ዋጋው የሚላከውም ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ብሔራዊ ባንክ፣ ከላኪዎች እና ከአቅራቢዎች ማኅበር፣ ከብሔራዊ ግብይት ፈጻሚዎች ማኅበር እንዲሁም ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ የተወከሉ የኮሚቴ አባላት ተነጋግረው መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም የአገራችንን የወጭ ንግድ በህግ እና በስርዓት እንዲከወን ያስችላል ብለዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here