“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
ገጸ ባህርያት በልቦለዳዊ ሥራዎችም ሆነ በኢ-ልቦለዳዊ ጽሑፎች ውስጥ የደራሲውን ምናባዊና እውናዊ ሐሳብ ወደ አንባቢና ተመልካች የሚያደርሱለት ‘ፍጡራን’ ናቸው። አንድ የኪነጥበብ ባለሙያ በእነዚህ ገጸ ባህርያት አማካኝነት ውስጣዊ ስሜትን፣ ቁጭትን፣ መልዕክትን፣ ትችትን እና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸውን ሐሳቦች አሁናዊነትን እና ትምቢታዊነትን በተላበሰ መልኩ ለአንባቢያንና ለአድማጭ ተመልካቾች ያደርሳል። ሐሳቡንም ያጋራል። ያመኑበትም ሐሳቡን ተግባራዊ ያደርጉታል። ያላመኑበትም ትምህርት ይወስዱበታል፤ ጠልተው ይነቅፉታል።
በአሁን ሰዓት በአገራችን እየታዩ ወይም እየተሠሩ ያሉ አገርኛ ፊልሞቻችን ላይ ሴቶች እየተሳሉ ያሉበት ገጸ ባህሪ አስደሳች አይደለም። በተጨማሪም ሴቶችን ዋና ገጸ ባህሪ አድርገው የሚያዘጋጁና በእነሱ ላይ ተመሥርተው የሚሠሩትም በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። የተሠሩትም ቢሆኑ ገጸ ባህሪ አሳሳላቸው አስተማሪ አይደለም።
ደራሲዎቻችን ሴቶችን በምናባቸው የሚያዩበት መነጽር የተዛባ ይመስለኛል። በብዛት የሚያተኩሩትም የውጪያዊው ውበት ላይ ነው። ውስጣዊ ማንነታቸውን በውጪያዊው የራስ ያልሆነ ማንነት ቀብተው ያልሆነ ማንነት ማሳየትን ዋነኛ ምርጫቸው ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
ውስጣዊ ማንነትን አጉልቶ ማሳየት ተገቢ ነው። ተመልካችንም አንባቢንም ሊያንጽ የሚችለው ውጫዊ አሳሳል ሳይሆን ውስጣዊ ቀረጻ ነው። ውጪያዊ ቀረጻ ዐይንን እንጂ ልብን አያስደስትም:: ውስጣዊ ቀረጻ ውስጥ ይቀራል። ውጪያዊ ቀረፃ ውጪ ይበተናል። ውስጣዊ አሳሳል ልብ ላይ ሲታተም ውጪያዊ አሳሳል ዐይን ላይ ይቀራል።
ዐይን ላይ የቀረ ደግሞ የመረሳት እድሉ ሰፊ ነው። ደራሲዎቻችንና አዘጋጆቻችን ዘላቂነት ያለው የጥበብ ሥራን መሥራት ከሻቱ ውስጣዊ ማንነትን የሚያንፀባርቁና ማንነትን የሚገልጹ አይረሴ ሴት ገጸ ባህርያትን ሊፈጥሩልንና በውስጣችን ሊያኖሩልን ይገባል።
በጥንቃቄ ያልተሳሉ ገጸ ባህርያት የሚመለከትና የሚያነብ ሰው በጥሩ ሁኔታ የተቀረፀ አመለካከትና ዕይታ አይኖረውም። ሴቶች በውበታቸው ብቻ የሚኮሩ፣ በራሳቸው የማይተማመኑ፣ የወንድ ጥገኛ የሆኑ፣ ደካማ አመራርን የሚያንፀባርቁ፣ ለበቀል የተፈጠሩ፣ በማኀበረሰቡ ተበድለው የኖሩ ብቻ አድርጎ መሳል የተሳሳተ አቅጣጫን ማመላከት ነው።
ሴቶችን ገንዘብ ወዳድ፣ መኪና አፍቃሪ፣ ውጪያዊ ግንባታን ወዳጅ፣ በሆነው ባልሆነው አልቃሻ አድርጎ መሳል ብዥታ የበዛበትን ስዕል ለኅብረተሰቡ ማቅረብ ነው። ይህን ጥበባዊ ሥራ የሚያነቡና የሚመለከቱ ሴቶች ላይም የእነሱ ያልሆነን ማንነት በግድ ለመጫንና ለመስጠት መፍጨርጨርም ነው። ሲጭኑት ቀላል ለማውረድ ግን አስቸጋሪ ጭነት።
በእርግጥ ፊልምም ሆነ ሌላ ሥነ ጽሑፋዊ ሥራ “የገሀዱ ዓለም ነፀብራቅ ነው” ይባላል። ቢሆንም ትክክለኛውን ገሀድ ማንፀባረቅም አለበት። ፈጠራዊ/ምናባዊ ቢሆንም መነሻው እውነታ ነው። እውነታው ደግሞ የሚታይ እውነታ ነው።
እናም ደራሲዎቻችን፣ ኪነ ጥበባዊ ሥራውን በመልካምነቱ ልንማርበት ሲገባ በቅሽምናው እንድንማርበት እድሉን ባትሰጡን መልካም ነው። መሳያችሁን አስተካክሉ። ትክክለኛውን ማንነት ለትክክለኛዋ ሴት ገጸ ባህሪ ሳሉ። በጥንቃቄ ያልተሳሉ ገጸ ባህርያት እኩይ ባህርያትን ቆርጠው አይጥሉም።
ደስታ ሽርካ (ደስታ ጠማኙ)
ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015


