በዘፈቀደ የሙያ ሥም መጠቀም ይቀራል ተብሏል
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኪነ ጥበብ ሙያ ተቋማት ማረጋገጫ እና የባለሙያዎች የሙያ ማረጋገጫ ሥርዓት ሊጀመር መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
በዚህም የኪነ ጥበብ የሙያ ዘርፎችን የሚያሠለጥኑ ተቋማትን ብቃት ማረጋገጥ የመጀመሪያው ሲሆን፣ በ11 የኪነ ጥበብ ሙያ ተቋማት ተቋማዊ የሙያ ማረጋገጫ ሥርዓት ለማስጀመር ሕጋዊ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል። የሙያ ተቋማት ማረጋገጫ ተግባራዊ እንደተደረገ፣ የሙያተኞች ሙያዊ ማረጋገጫ ሥርዓት ወደ ተግባር እንደሚገባ ተመላክቷል።
የሙያ ማረጋገጫ ተግባራዊ የሚደረግባቸው የኪነ ጥበብ ተቋማትም የሙዚቃ፣ ስዕል፣ ቴአትር፣ ፊልም፣ ቅርጻ ቅርጽ፣ ኮሜዲ፣ ፋሽንና ሞዴሊንግ፣ ዲጄ፣ ድርሰት፣ ሰርከስ እና ውዝዋዜ ናቸው ተብሏል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብ እና ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማሃዲ ሙያተኛ ከመኖሩ በፊት ተቋም ሊኖር ይገባል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የኪነ ጥበብ ሙያዎችን ለማሠልጠን ተቋሙ ብቁ ነው ወይ የሚል የማረጋገጥ ሥራ በቅድሚያ እንደሚሠራም ነፊሳ ጠቁመዋል።
ይህን ለማድረግም የብቃት መለኪያ መስፈርቶች በሰነድ ተዘጋጅተው ከባለድርሻ አካላት ጋር በውይይት ከዳበሩ በኋላ የሕግ ማዕቀፍ ሆነው እንደሚተገበሩ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል። ከሚመለከታቸው የሙያ ዘርፎች እንዲሁም የተለያዩ አካላትን በማሳተፍ በተዘጋጀው ሰነድ ላይ ግምገማ ከተካሄደ በኋላ፣ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚላክም ተመላክቷል።
በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ከተሰጠበት በኋላ፣ ማንም አካል እንደፈለገ የሙዚቃ፣ የስዕል ወይም የሌላ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ተቋም ነኝ ማለቱ እንደሚቀር ነፊሳ ጠቁመዋል። እስካሁን ባለው ጊዜ የሙያ ተቋማት ብቁ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ ሥርዓት አልነበረም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ከዚህ በኋላ ግን ይህን የሚቀርፍ ሥራ ለመሥራት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
‹‹አንድ መጽሐፍ የጻፈም ሆነ ኻያ መጻሕፍት የጻፈ ደራሲ እየተባለ ነው›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ የማረጋገጫ ሥርዓቱ ተግባራዊ ሲደረግ አንድ ሰው ደራሲ ለመባል ምን ምን መስፈርቶችን ማሟላት እንደሚገባው በግልጽ ይደነገጋል ብለዋል።
የኪነ ጥበብ የሙያ ዘርፎች ተመሳሳይ አካሄድ እንደሚኖር የተገለጸ ሲሆን፣ ለባለሙያዎች ከጀማሪ እስከ ከፍተኛ ድረስ በደረጃ የሙያ ማረጋገጫ የሚሰጣቸው መሆኑም ተመላክቷል። ይህም የቀደምት ሙያተኞችን ሞራል ለመጠበቅ እንደሚረዳ ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ የተናገሩት። በተጨማሪም ማንም ሰው እንደፈለገ ራሱን ባለሙያ አድርጎ መጥራቱን እንደሚያስቀር እና አገሪቱም ከዘርፉ የምታገኘውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለማስጠበቅ እንደሚበጅ ጠቁመዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር በተያዘው በጀት ዓመት ይህን የማሳካት ዕቅድ እንዳለው እና ሰነድ አዘጋጅቶ ወደ ብቃት ማረጋገጫ ሥርዓቱ ለመግባት በዝግጅት ላይ ነው ብለዋል። ከተቋማት ማረጋገጫ ሥርዓት ቀጥሎ ይተገበራል የተባለው የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የሙያ ማረጋገጫ በእያንዳንዱ ሙያ ላይ ዝርዝር የሙያ መስፈርት የሚያስቀምጥ ነው ተብሏል።
የሙያ ማረጋገጫው በሕግ ማዕቀፍ ተደግፎ ተግባራዊ መደረግ ከተጀመረ በኋላ፣ በሕጉ መሠረት መስፈርቱን አሟልቶ የሙያ ማረጋገጫ የሌለው ሰው በዘርፉ ሙያተኛ ተብሎ መጠራት እንደማይችል ተመላክቷል።
በ2015 ቢያንስ የኪነ ጥበብ ሙያዎችን የሚያሠለጥኑ ተቋማትን የሚመዝን የተቋማት ማረጋገጫ ሥርዓት እንደሚያልቅ የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ከዚህ በኋላ የኪነ ጥበብ ዘርፉ በሕግ እንደሚመራ ጠቁመዋል።
በዚሁ ዘርፍ ላይ የተለያዩ ሽልማቶችን የሚያዘጋጁ ግለሰቦችና ተቋማት ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሽልማት እንዲሰጡ ፈቃድ እንዳልተሰጣቸው ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል። የማረጋገጫ ሥርዓቱ ሲዘረጋ ሽልማት የሚሰጡ ግለሰቦችም ይሁኑ ተቋማት ፈቃድ ካልተሰጣቸው ሽልማት መስጠት እንደማይችሉም ተመላክቷል።
ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015


