በገርባ ጉራቻ ከታፈኑት 11 የቤተክርስቲያን አገልጋዮች መካከል ሦስቱ በድርድር መለቀቃቸው ተሰማ

0
988

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን ኩዩ ወረዳ በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ከታገቱ 11 የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ሦስቱ በድርድር ገንዘብ ተከፍሎ መለቀቃቸው ተሰማ።

ጥቅምት 19/2015 ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ በሽብርተኝነት የተፈረጀው የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ናቸው በተባሉ ሰዎች ታፍነው ከተወሰዱት 11 የምድረ ገነት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች መካከል ሦስቱ ረቡዕ ጥቅምት 23/2015 ወደ ቀያቸው ተመልሰው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀላቸውን አዲስ ማለዳ ከዐይን እማኞች ሰምታለች።

አገልጋዮቹ ጥቅምት 19 ሲታፈኑ የደብሩ አገልጋይ የሆነ አንድ ዲያቆን መገደሉ ይታወሳል። ምሽት ከአምስት ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ወደ ደብሩ የኦነግ ሸኔ አባላት ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች በመግባት ማኅሌት ሊቆሙ ከተገኙ አገልጋዮች መካከል አንደኛውን ገድለው 11ዱን ማገታቸው የሚታወስ ነው። ታፍነው ከተወሰዱት አገልጋዮች መካከል የደብሩ አስተዳዳሪ ይገኙበታል። የተቀሩት ታፋኞች ሦስቱ ካህናት ሲሆኑ፣ ሦስቱ ደግሞ የደብሩ የጥበቃ ሠራተኞች ናቸው፣ የተቀሩት አራቱ ደግሞ ዲያቆናት ናቸው።

ይህ ዘገባ እስከ ተጠናከረበት ሐሙስ ጥቅምት 24/2015 ምሽት ድረስ አዲስ ማለዳ ማጣራት እንደቻለችው አስተዳዳሪው እና ኹለት ዲያቆናት ከታገቱበት ተለቀዋል። ታጋቾቹ የተለቀቁት ገንዘብ ተከፍሎ መሆኑም ተሰምቷል። የተለቀቁት አገልጋዮች ምንም ዓይነት አካላዊ ጉዳት እንዳልደረሰባቸውም ለማወቅ ተችሏል።

አዲስ ማለዳ ማጣራት እንደቻለችው የተቀሩትን ሦስቱን ካህናት፣ ሦስት ጥበቃዎች እና ኹለት ዲያቆናትን በተመሳሳይ መንገድ ለማስለቀቅ ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል።

በተያያዘ ዜና ከዚህ ክስተት አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ከገርባ ጉራቻ ከተማ በ20 ኪሎሜትር ገደማ ርቅት ላይ በምትገኘው ብሪቲ ከተማ የቢርቢርሳ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የሆኑ አምስት ካህናት በተመሳሳይ በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ታፍነው የተወሰዱ ሲሆን፣ ከቀናት በኋላ መለቀቃቸው ተሰምቷል።

ለአዲስ ማለዳ የነገሯት የብሪቲ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት፣ ብሪቲ ከተማ ለቀናት በሸኔ ታጣቂዎች ተይዛ ነበር። በተያዘችባቸውም ቀናት ከከተማዋ በርካታ ሰዎች ታፍነው ተወስደዋል። ቀደም ባለው ጊዜም ከአካባቢው ታፍነው ተወስደው የተገደሉ እና ይሙቱ ይኑሩ የማይታወቅ ሰዎች መኖራቸውንም ለማወቅ ተችሏል። በአሁን ሰዓት የብሪቲ ከተማን የመከላከያ ሠራዊት አባላት ደርሰው ነፃ ያወጧት መሆኑንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። ታጣቂዎቹ ከተማዋን እንደያዙ የብዙ ሰዎች ቤት መዘረፉና መውደሙም ተሰምቷል።

ከገርባ ጉራቻ ከተማ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ በጥቅሉ በሰሜን ሸዋ ሰላሌ ዞን ወረዳዎች በርካታ የገጠር ቀበሌዎች በኦነግ ሸኔ ቁጥጥር ስር ናቸው። በከተሞች ያሉት ዜጎችም በከፍተኛ የደኅንነት ስጋት ውስጥ ይገኛሉ።

ጥቅምት 19 በገርባ ጉራቻ ከተማ ታፍነው የተወሰዱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ሲሆኑ፣ በአካባቢው በሽብረተኝነት በተፈረጀው የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ቤተ እምነቶች ላይ ጥቃት ማድረሱን ነዋሪዎች ይናገራሉ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ለጥቅምቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጠቅላላ ጉባኤ ባቀረበው ሪፖርት በዞኑ ካሉ 16 ወረዳዎች በስምንቱ አብያተ ክርስቲያናቱ በኦነግ ሸኔ ጥቃት ሙሉ በሙሉ መዘጋታቸውን አመላክቷል።

በሰሜን ሸዋ ሰላሌ ዞን በወቅታዊ የጸጥታ እና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ከዞኑ ባለሥልጣናት መረጃ ለማግኘት አዲስ ማለዳ ያደረገችው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።


ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here