ከኹለት ዓመት ጦርነት ወደ ሠላም!

0
1649

ኸለት ዓመቱን ሊደፍን አንድ ቀን ሲቀረው ነበር፤ በሕወሓት ቡድን እና የፌዴራል መንግሥት መካከል ሲጠበቅ የነበረው ድርድርና የሰላም ስምምነት እውን የሆነው። ይህም ብዙዎችን ደስ ያሰኘና ተጨንቀው ለነበሩት እፎይታ የሰጠ ሆኗል። ከዚህ በኋላ ሊደርሱ የሚችሉ ኪሳራዎችን፣ መፈናቀልና ሞቶችንም የሚያስቀር ነው።

ከዚህ በኋላም ትልቁ የቤት ሥራ የሚሆነው አፈፃፀሙ ላይ መሆኑ እሙን ነው። አንዳንዶች በዚህ ዙሪያ ስጋት እንደሚገባቸው በተለያየ አጋጣሚ ሲገልፁ ይስተዋላል። በአንፃሩ ስምምነቱ በተገባ መንገድ ተግባራዊ እንዲሆንና የታለመው ሰላም እንዲመጣ፣ ከድርድር ፈፃሚዎች ጀምሮ ከሁሉም ዜጋ ብዙ እንደሚጠበቅ በተደጋጋሚ ሲነገር እየተሰማ ነው። አደራዳሪዎችን የስምምነቱን ተፈፃሚነት ነገር አደራ ብለዋል። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ይህን ጉዳይ መነሻ በማድረግ፣ በስምምነቱ የተካተቱ ነጥቦችንና ቀጣይ የሰላም ሂደቶችን በተመለከተ እንደሚከተለው የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ከኹለት ዓመት ደም አፋሳሽ ጉዞ በኋላ፣ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት በተካሄደው ድርድር የኢትዮጵያ መንግሥት እና የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ተወካዮች በዘላቂነት ጦርቱን ለማቆም ተስማምተዋል። በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው ድርድር ኹለቱ ኃይሎች ጦርነት ለማቆም ስምምነት ላይ መድረሳቸው በጦርነቱ ሊደርሱ የሚችሉ ተጨማሪ ኪሳራዎችን የሚያስቀር በመሆኑ ብዙዎች እያደነቁት ነው።

ለኹለት ዓመታት የዘለቀው ጦርነት መነሻውን በትግራይ ክልል ያድርግ እንጂ፣ በአማራና በአፋር ክልል ተስፋፍቶ በሦስቱ ክልሎች ከሰብዓዊ ቀውስ እስከ ሀብት ውድመት ዘርፈ ብዙ ኪሳራ አስከትሏል። ምንም እንኳን የጦርነት ቀጠና በሆኑት የሦስቱ ክልል አካባቢዎች ላይ የደረሰው ጉዳት  የጎላ ቢሆንም፣ ጦርነቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እንደ አገር በኢትዮጵያ ላይ ዘርፈ ብዙ ኪሳራ ያስከተለ ነበር። ይህንኑ አክሳሪ ጦርነት ለማስቆም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተካሄደው ድርድር የጦርነቱ ዋና ተዋንያን በሆኑት በኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕወሓት መካከል ጦርነቱን ለማቆም ስምምነት ላይ ተደርሷል።

በኹለቱ ኃይሎች መካከል ጦርቱን በዘለቂነት ለማቆም ስምምነት ላይ መድረሳቸው ለኹለት ዓመት የዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዳይቀጥል ከማድረጉ ባሻገር፣ በጦርነቱ ምክንያት ሰብዓዊ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ እድል ይፈጥራል።

ኢትዮጵያ ከኹለት ዓመት በፊት የገጠማት ጦርነት በሠላም እልባት እንዲያገኝ ከአገር ዐቀፍ ተቋማት እስከ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት ጥረት ሲያደርጉ ነበር። በተለይ አፍሪካ ኅብረት የሰሜኑ ጦርነት በሰላማዊ ንግግር እንዲቋጭ ከአንድ ዓመት በላይ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ነበር። የኅብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴንጉን ኦባሳንጆ በተደጋጋሚ የፌዴራል መንግሥትንና የሕወሓትን ባለሥልጣናት በተናጠል ሲያነጋግሩ ቆይተዋል። ከአፍሪካ ኅብረት ጥረት በተጨማሪ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ  አምባሳደር ማይክ ሐመር ከመቀሌ አዲስ አበባ እየተመላለሱ ኹለቱን ኃይሎች በተናጠል ሲያነጋግሩ ነበር።

የደቡብ አፍሪካው ድርድር በአፍሪካ ኅብረት መሪነት የተካሄደ ቢሆንም፣ የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርድት (ኢጋድ)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እና የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ የሰላም ሂደት ላይ በታዛቢነት ተሳታፊ ሆነዋል። ኅብረቱ ድርድሩን እንዲመሩ የሰየማቸው የኅብረቱ አፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴንጉን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞው የኬኒያ ፕሬዝደንት ኡህሩ ኬኒያታና የቀድሞዋ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝደንት ፋምዚሌ ምላምቦ ንግኩሳ  ድርድሩን መርተዉታል።

ኅብረቱ ኹለቱን ተፋላሚ ኃይሎች ለማቀራረብና ወደ ንግግር ለማስገባት ረዥም ጊዜ የፈጀበት ቢሆንም፣ ከብዙ ጥረት በኋላ ጥቅምት 15/2015 በደቡብ አፍሪካ የተጀመረው ድርድር ለተከታታይ 10 ቀናት ከተካሄደ በኋላ ጥቀምት 23/2015 በጦርነቱ ኹለተኛ ዓመት ዋዜማ ላይ ለስምምነት በቅቷል።

ስለ ስምምነቱ

በአፍሪካ ኅብረት ዋና አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ ለ10 ቀናት የተካሄደው ድርድር ለስምምነት ከበቃ በኋላ፣ ኹለቱ ኃይሎች የተስማሙባቸው ጉዳዮች በድርድሩ መሪ በአባሳንጆ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ተደራዳሪ በሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንና የሕወሓት ተደራዳሪ በሆኑት በጌታቸው ረዳ በኩል በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ለሕዝብ ይፋ ሆኗል። በድርደሩ ኹለቱም ኃይሎች ስምምነት ላይ የደረሱባቸው ጉዳዮች ጦርነቱን በዘላቂነት ከማቆም የጥላቻ ፕሮፖጋንዳን እስከማቆም የሚደርሱ ናቸው።

ኹለቱ ኃይሎች አስቸኳይ የተቃርኖ አካሄዶችን እና ውጊያዎችን ማቆም የስምምነቱ አካል ሲሆን፣ ከውጭ ኃይሎች ጋር ማበር፣ የአየር ጥቃቶችን መፈጸም፣ ፈንጂዎችን መትከል፣ ድንገተኛ ጥቃቶችን መፈጸም እንዲያቆሙ በስምምነት ሰነዱ ላይ ተመላክቷል። በዚህም በትግራይ ክልል ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲመለስ እና የፖለቲካ ውይይት እንዲጀመር ማስቻል፣ እና የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ የፌዴራል ሥልጣን ወደ መቀሌ ከተማ እንዲመለስ እና አስፈላጊው ሕዝባዊ አገልግሎት እንዲቀጥል ማስቻል ከኹለቱ ኃይሎች ይጠበቃል።

ሌላኛው የስምምነት ነጥብ የሕወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ መፍታት ሲሆን፣ በዚህም መሠረት “ኢትዮጵያ አንድ የአገር መከላከያ ሠራዊት ብቻ ነው ያላት” በሚለው ጉዳይ ተስማምተዋል። ኹለቱ ኃይሎች “መሬት ላይ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የሕወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ የሚፈቱበት፣ የሚበተኑበት እና ወደ ማኅበረሰቡ ተመልሰው የሚቀላቀሉበት ዝርዝር ፕሮግራም ላይ ተስማምተናል” ብለዋል። የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማረጋገጥ እና መጠበቅ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን የተስማሙት ሕወሓት እና የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትን ለማስከበር ተስማምተዋል።

በዚህም ስምምነቱ በተፈጸመ በ24 ሰዓት ውስጥ በኹለቱም ወታደራዊ ኮማንደሮች መሀል ግንኙነት እንዲፈጠር፣ በአምስት ቀናት ውስጥ ደግሞ ውይይት እንዲያደርጉ መስማማታቸው በስምምነት ሰነዱ ላይ ተመላክቷል። የትጥቅ አፈታቱ ሂደት ለከባድ መሣርያዎች ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲከናወን፣ ሂደቱም ኮማንደሮቹ ከተገናኙ በኋላ በ10 ቀን እንዲጠናቀቅ፣ ትንንሽ መሣሪያዎችን ጨምሮ ሁሉም ትጥቅ አፈታት በአንድ ወር ውስጥ እንዲጠናቀቅና የትጥቅ አፈታት ሂደቱ በትግራይ ክልል ያለውን የሕግ እና ጸጥታ ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ እንዲፈጸም በስምምነቱ ላይ ተካቷል።

ሌላኛው ወሳኝ ስምምነት የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰብዓዊ ድርጅቶች ጋር በመሆን የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የተፋጠነ እርዳታ እንዲያደርስ ኹለቱ ኃይሎች መስማማታቸው ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለመጀመር ጥረቱን ለመቀጠል እና በግጭቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመጠገን ከስምምነት ደርሰዋል።

በትግራይ ክልል ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የሚሰፍንበት እርምጃዎች፣ ፖለቲካዊ ልዩነትን የሚፈታ ማዕቀፍ እና ተጠያቂነትን፣ እውነትን፣ እርቅ የሚያመጣ የፍትሕ የሽግግር ሥርዓት ፖሊሲ ማዕቀፍ ለማረጋገጥ ተስማምተዋል። ሕወሓት የፌዴራል መንግሥቱን ሥልጣን እንዲያከብር፣ የፌዴራል ንብረቶችን፣ ተቋማትን እና ዓለም አቀፍ ድንበር እንዲቆጣጠር ማስቻል የስምምነቱ አካል ሲሆን፣ ሕወሓት በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ ተጻራሪ ቡድኖችን መደገፍ እንዲያቆም፣ ጸረ ሕገ መንግሥታዊ የሥርዓት ለውጥ ሙከራ እንዳያደርግ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕወሓት ላይ ጥሎት የነበረው የሽብርተኝነት አዋጅ እንዲነሳ በደቡብ አፍሪካው ድርድር ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን፣ የሕወሓት ሽብርተኝነት እንደተነሳ በሳምንቱ ኹለቱ አካላት የፖለቲካ ውይይት እንዲጀምሩ እና ለፖለቲካ ልዩነታቸውን መፍትሔ እንዲያበጁ በስምምነቱ ተካቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትግራይ ክልል ምርጫ አካሂዶ የክልልና የሕዝብ ተወካዮች እስከሚመረጡ ድረስ፣ በክልሉ አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲጀመር ኹለቱ ኃይሎች የተስማሙ ሲሆን፣ የውዝግብ መንስኤ የሆኑ የአካባቢ ይገባኛል ጥያቄዎችን በሕገ መንግሥቱ መሠረት እልባት እንዲያገኙ ተስማምተዋል።

ስምምነቶቹን ተግባራዊ ለማድረግ ኹለቱ አካላት የትኛውንም ዓይነት ግጭት ለማቆም፣ ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ ፕሮፖጋንዳዎች ለመታቀብ ተስማምተዋል። ኹለቱ አካላት የሚያወጧቸው መግለጫዎች ይህን ስምምነት የሚደግፉ ብቻ እንዲሆኑ ተስማምተዋል። በኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ዜጎች ይህን ስምምነት እንዲደግፉ፤ ከፋፋይ እና ጥላቻ ከሚነዙ አስተያየቶች እንዲቆጠቡ እና ለመልሶ ግንባታ የሚውሉ ሀብት እንዲያሰባስቡ ጥሪ ቀርቧል።

የድርድሩ መሪ ኦሊሴጎ ኦባሳንጆ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕወሓት በደቡብ አፍሪካ ባደረጉት የሰላም ስምምነት በተፈራረሙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ ሰላም፣ ደኅንነት እና መረጋጋት ለማምጣት ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል። አፍሪካ ኅብረት ከሾማቸው 14 ወራት እንዳስቆጠረ ያስታወሱት ኦባሳንጆ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የክልል መሪዎችን እና ባለድርሻ አካላትን፣ በሌሎች የኢጋድ አባል አገራት፣ በአፍሪካ ውስጥ እና ከአፍሪካ ውጪ ካሉ የልማት አጋሮች ጋር ምክክር ማድረጋቸውን ጠቁመዋል። የሰሜኑን ጦርነት በሰላማዊ ንግግር ለመፍታት ባደረጉት ጥረት ወደ ትግራይ ክልል ስምንት ጊዜ ጉዞ ማድረጋቸውን አንስተዋል።

ኦባሳንጆ ስለ ስምምነቱ ባደረጉት ንግግር፣ “ዛሬ ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካ ቀንድ ብሎም ለአፍሪካ በአጠቃላይ አዲስ ንጋት ጀምሯል” ሲሉ ተደምጠዋል። ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች የሚለውን መርህ ተግባራዊ እያደረግን ነው ያሉት ኦባሳንጆ፣ በኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ ዋና ተዋናይ የሆኑት ኹለቱ ኃይሎች ጦርነቱ እንዲቆም፣ ትጥቅ እንዲፈታ፣ ሕግና ስርዓትን ወደ ቀድሞው ሁኔታ መመለስ፣ አገልግሎትን ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ፣ የሰብዓዊ አቅርቦቶችን ያለማቋረጥ ተደራሽ ለማድረግ፣ ሰላማዊ ዜጎችን በተለይም ሴቶችን ለመጠበቅ ተስማምተዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕወሓት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ያደነቁት ኦባሳንጆ፣ “ይህ ወቅት የሰላም ሂደት መጨረሻ ሳይሆን፣ የመጀመርያው ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። አክለውም፣ በኹለቱ ኃይሎች መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት ተግባራዊ መሆን ለሂደቱ ስኬት ወሳኝ ነው ብለዋል።

የሰላም ስምምነቱን የተለያዩ አካላት በበጎነት የተቀበሉት ሲሆን፣ የሰላም ተግባራዊነት በተሳካ ሁኔታ እንዲፈጸም ኹለቱ ኃይሎች እና የባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑ እየተገለጸ ነው። ስለ ስምምነቱ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ የሰጡት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) የሰላም ስምምነቱን ምክር ቤታቸው እንደሚያደንቅ ጠቁመዋል።

ለኹለት ዓመት በዘለቀው ጦርነት ብዙ ኪሳራ መድረሱን የሚያስታውሱት ሰብሳቢው፣ የሰላም ስምምነት መፈጸሙ ተጨማሪ ኪሳራ ውስጥ ከመግባት የሚታደግ መሆኑን ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ የተፈጸመው የሰላም ስምምነት በአግባቡ ተግባራዊ ተደርጎ የሚፈለገውን ሰላም እንዲያመጣ ሂደቱን በጥንቀቄ መምራት እንደሚገባ ይመክራሉ።

ለሰላሙ ስኬት

ከጦርነት በኋላ የሰላም ሂደቶች መኖራቸው የተለመደ ቢሆንም፣ የሰላም ስምምነቶች በሚፈጸሙበት ወቅት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ሊያጋጥሙ የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚኖር ጥናቶች ያመላክታሉ። በርግሆፍ ፋውንዴሽን የተባለ ተቋም ስለ የሰላም ሂደት ጽንሰ ሐሳብ ምንነት በድረ ገጹ ባሰፈረው ማብራሪያ፣ የሰላም ሂደት በኹለት ቡድኖች መካከል ጦርነትን ወይም ሁከትን ለማስወገድ የተነደፉ ተከታታይ ንግግሮች፣ ስምምነቶች እና ተግባራትን ያካትታል ይላል። ፋውንዴሽኑ የሰላም ሂደቶች መደበኛ እና መደበኛ ያልሆኑ ስልቶችን ሊያካትቱ እንደሚችሉ እና ብዙ ተዋናዮችን የሚሳተፉበት የረዥም ጊዜ ሥራ መሆኑን ያብራራል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢው እንደሚሉት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕወሓት የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት ተፈጻሚነት በእቅድ በታገዘ ሥርዓት ሊመራ የሚገባው መሆኑን ያነሳሉ። የሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ሂደቱ ረዥም ጊዜ ሊፈጅ እንደሚችል የሚገልጹት ሰብሳቢው፣ አፈጻጸሙ የሕዝብና የመንግሥትን ብርቱ ትብበር የሚጠይቅ መሆኑን ያነሳሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት በፖለቲካ አመራሮች የተፈጸመው ስምምነት ወደ ታች ወርዶ ተፈጻሚ በሚሆንበት ወቅት በጦርነቱ ከተስተናገዱ ውስብስብ ችግሮች አንጻር የስምምነቱ አፈጻጸም ላይ እንቅፋት ሊገጥም እንደሚችል በማንሳት ነው።

የሰላም ስምምነቱን የመተግበር ሂደቱ ላይ ችግሮች ሊገጥሙ እንደሚችሉ በማሰብ በጥብቅ ትብብርና እቅድ ስምምነቱን አስፈጽሞ የሚጠበቀውን ሰላም ለማምጣት የበርካታ ባለድርሻ አካላትን ትብብር እንደሚፈልግም ሰብሳቢው ይገልጻሉ።

በጦርነቱ በዜጎች ላይ የተከሰቱ ችግሮች በአፈጻጸሙ ላይ ተግዳሮት እንዳይፈጥሩ፣ በጦርነቱ ተደራራቢ ችግር ያስተናገዱ የማኅበረሰብ ከፍሎችን መልሶ የማቋቋምና ተገቢውን ካሳ በመፈጸም፣ እንዲሁም ከደረሳበቸው የሞራልና የሥነ ልቦና ችግር እንዲያገግሙ መሥራት እንደሚገባ መብራቱ ጠቁመዋል። ተጎጂ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከደረሰባቸው ችግር እንዲያገግሙ ከማገዝ ጎን ለጎን፣ ፖለቲከኞች፣ የመንግሥት አካላት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ሕዝቡ ስለሰላም እና ስለ አንድነት የሚሰብኩ ሥራዎች ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ዓለሙ ይገልጻሉ።

“ሠላም ከጦርነት ይሻላል” የሚሉት ዓለሙ፣ በየትኛውም ሁኔታ ከጦርነት በኋላ ፖለቲከኞች እጅ ለእጅ መጨባበጣቸው የተለመደ መሆኑን በመገንዘብ፣ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ላይ የሚፈጠረውን ተጽዕኖ የሆነው ሁሉ ለሰላም የተከፈለ ዋጋ መሆኑን ማስገንዘብ እንደሚገባ ጠቁመዋል። በጦርነቱ ጉዳት ያስተናገዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ለማከም፣ ግጭቱ በፖለቲከኞች መካከል የተደረገ መሆኑን ማስገንዘብና ሕዝብ ከሕዝብ ጋር ችግር እንደሌለበት ግንዛቤ መፍጠር አንዱ የሰላም ሂደት አካል መሆን አንዳለበትም አክለዋል።

የሕዝብ ለሕዝብ ትብብር ለሰላም ስምምነቱ ወሳኝ መሆኑን የሚያነሱት መብራቱ፣ በጦርነቱ የደረሱ ችግሮችን በይቅርታ በማለፍ ወደ ፊት መሄድ ላይ በአንክሮት መሥራት ከኹሉም ባለድርሻ አካል የሚጠበቅ የቤት ሥራ መሆኑን መብራቱ አመላክተዋል። ለአገር ሲባል ችግሮችን በጋራ ትብብር መፍታት ከሁሉም ባለድርሻ አካል የሚጠበቅ መሆኑን እና ችግሮችን በሂደት በምክክርና በእርቅ መፍታት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አንዳንድ ወገኖች በስምምነቱ ተፈጻሚነት ላይ የተለያዩ ምክንያቶችን በማንሳት ስጋት እንዳላቸው እየገለጹ ነው። ከስጋቶቹ መካከል ከረዥም ዓመታት የውዝግብ መንስኤ የሆኑ የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎች የሚፈቱበት ሁኔታ እና የኤርትራ በጦርነቱ ተሳታፊ መሆን ይገኙበታል።

የኤርትራ ኃይል የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ በጦርነቱ ተሳታፊ በመሆኑ፣ የሚነሱ ስጋቶች ተገቢ መሆናቸውን መብራቱ ይገልጻሉ።  የኤርትራ ኃይል ጣልቃ ገብነት ከስምምነቱ በኋላ በምን ሁኔታ እንደሚቀር ስጋት መፍጠሩ የሚጠበቅ ነገር ነው ይላሉ። ከዚህ አንጻር የሚታየውን ስጋት በአግባቡ ለማስተናገድ የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ መንግሥት ጋር ዲፕሎማሲ ንግግር አድርጎ የኹሉቱ አገሮች መከላከያ በየድንበራቸው እንዲመለሱ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኤርትራ ኃይል ከኢትዮጵያ ወጥቶ የራሱን ድንበር መያዝ አለበት የሚሉት መብራቱ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል የራሱን ድንበር መያዝ እንዳለበት ጠቁመዋል። አገራት መመራት ያለባቸው በመርህና በስምምነት መሆኑን ያነሱት መብራቱ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን ማጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል፣ ለሰላም ስምምነቱ እንደ ስጋት የታየው በተለይ በአማራ እና በትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚነሳው የወሰን ይገባኛል ጥያቄ ሲሆን፣ የወሰን ጥያቄዎች በሕገ መንግሥቱ መሠረት እልባት ማግኘት እንዳለባቸው በደቡብ አፍሪካው ስምምነት ላይ ተመላክቷል። የኢትዮጵያ መንግሥትም የወሰን ጥያቄዎችን በሕግ መንግሥቱ መሠረት እልባት እንደሚሰጣቸው አስታውቋል።

መብራቱ እንደሚሉት፣ የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት ያለባቸው ቢሆንም፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የአካባቢውን ሕዝብ ፍላጎት ባከበረ ሁኔታ መፈጸም እንዳለበት ጠቁመዋል። የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎች ወደ ሕዝብ ውሳኔ ሊመሩ እንደሚችሉ የሚገልጹት ዓለሙ፣ በሥርዓት ላይ የተመሠረተ ሥራ መሥራት ይገባል ብለዋል።

የሰላም ስምምነቱ እንቅፋት እንዳይገጥመው ሂደቱን በጥንቃቄ ከመምራት በተጨማሪ፣ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የፖለቲካ መረጋጋትና መተማመን መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።


ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here