በአማራ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች፣ የተሟላ ድጋፍ ለማቅረብ መቸገሩን የክልሉ አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
ኮሚሽኑ በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል ከ850 ሺሕ በላይ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች መኖራቸውን ጠቅሶ፣ በተለይም ሕወሓት በፈጠረው ቀውስ የተነሳ ምግብ ነክ የሆኑና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሰብዓዊ ድጋፎችን የሚሹ ከ8 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እንዳሉ አስታውቋል።
ይህን ተከትሎም፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ የተሟላ ድጋፍ ማቅረብ እንዳልተቻለ ያነሳው ኮሚሽኑ፣ የትራንስፖርት ችግር፣ የጸጥታ ሁኔታ እንዲሁም የሩስያና ዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ የተፈጠረው የምግብ እጥረትና የዋጋ ቀውስ ዋነኛ እንቅፋቶች መሆናቸውን አስገንዝቧል።
ሆኖም ችግሩን ለፌዴራል መንግሥት በማቅረብ፣ ለ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሕዝብ ድጋፍ ማድረስ መቻሉን የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢያሱ መስፍን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል፣ የክልሉ መንግሥት ከራሱ በጀት እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትን በማስተበበር ድጋፉ እየተቆራረጠም ቢሆን እየቀረበ ይገኛል ነው ያሉት። ኃላፊው አክለውም፣ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ጋር ያለው ችግር ከወራት በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር አሁንም ከፍተኛ የሆነ ችግር ነው ያለው ሲሉ ገልጸውታል። ጦርነቱ ከክልሉ የወጣው በቅርብ በመሆኑ፣ በአንድ በኩል ድጋፍ ሲደረግ በሌላ በኩል በርካታ ሰው ተፈናቅሎ ወደ ክልሉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በዚህም በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚቀርበው ድጋፍ፣ ወቅቱን የጠበቀና በቂ ነው ለማለት አያስደፍርም ያሉት ኃላፊው፣ የተሟላ ባለመሆኑም ለምሳሌ ስንዴ ሲቀርብ ዘይትና ጥራጥሬ ይጎድላል ብለዋል።
በክልሉ ሰብዓዊ ድጋፍ እያቀረቡ ያሉ ዓለም ዐቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ቢኖሩም፣ ቁጣራቸው ጥቂት መሆኑን አክለዋል። በክልሉ ከሚገኙ 850 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች ውስጥ ከ250 ሺሕ የሚልቁት በጦርነቱ ምክንያት (በቅርቡ ነጻ ከወጡት አካባቢዎች የተፈናቀሉትን ሳይጨምር) የተፈናቀሉ መሆናቸውን በማንሳት፣ ከ600 ሺሕ የሚበልጡት ደግሞ ከአጎራባች ክልሎች ማንነትን መሠረት አድርጎ በተፈጠረ ጥቃት የተፈናቀሉ መሆናቸውን ሳይጠቅሱ አላለፉም።
ለዚህም በአገራችን አስተማማኝ ሰላም ሲፈጠር፣ ከመጡበት ክልል ጋር በመነጋገር ችግር ፈች የሆነ የመልሶ ማቋቋም ተግባር ይከናወናል ብለን ተስፋ አድርገን እየሠራን ነውም ብለዋል። ከቅርቡ ነጻ በወጡ የአማራ ክልል አካባቢዎች ተፈናቅለው የቆዩ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
ለአብነትም በሰሜን ወሎ ዞን፣ በጃራ እና በመርሳ የነበሩ የአላማጣ እንዲሁም የራያ ዙሪያ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት። በሰሜን ጎንደር ዞንም እንዲሁ ከሕወሓት ነጻ በወጡ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደቀያቸው የመመለስ ተግባር እየተከናወነ ሲሆን፣ ከተመለሱ በኋላም ሰብዓዊ ድጋፍ የማቅረቡ ሥራ የሚቀጥል ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል።
ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015


