አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለግል ተማሪዎች የትምህርት ክፍያ ላይ የ100 በመቶ ጭማሪ ማድረጉ ከተማሪዎች ቅሬታ ቀርቦበታል።
በዚህም ከፍተኛ ቅሬታ አድሮብናል ያሉት ተማሪዎቹ፣ በተለይ በዚህ ዓመት ለመማር እቅድ ይዘው የነበሩ አዲስ ተመዝጋቢዎች፣ የመግቢያ ፈተናውን ከተፈተኑ በኋላ የዋጋ ጭማሪውን ሲመለከቱ ብዙዎች ማቋረጣቸውን ተናግረዋል።
በማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ኹለተኛ ዲግሪዋን ለመማር የተመዘገበች ተማሪ እንደገለጸችው፣ ተማሪዎች የመጀመሪያውን መግቢያ ፈተና 600 ብር ከፍለው ከተፈተኑ በኋላ፣ ያለፉት ኹለት ወር ገደማ ጠብቀው ለዲፓርትመንት መግቢያው ድጋሜ ከፍለው ይፈተናሉ።
ይሁን እንጂ፣ ይህንም ፈተና አልፈው የትምህርት ክፍያው በእጥፍ መጨመሩን ሲመለከቱ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ብዙዎች አቋርጠዋል ነው ያለችው። ዩኒቨርሲቲው ዋጋ መጨመሩን ቀድሞ ባለማሳወቁም ብዙዎች ሌላ ዩኒቨርሲቲ እንዳይመዘገቡ እንኳን ጊዜያቸውን አባክኗልም ብላለች።
ለአብነትም ባለፈው ዓመት ለ1 ‹‹ECTS›› (ECTS በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች አጠራር ክሬዲት ሐወር እንደማለት ነው) ክፍያ፣ 400 ብር የነበረው ዘንድሮ 800 ብር ሆኗል ብላለች።
በመሆኑም፣ በአንድ መንፈቀ ትምህርት 36 ‹‹ECTS›› የሚወስድ ተማሪ፣ ባለፈው ዓመት ይከፈል ከነበረው 14 ሺሕ ብር ገደማ ዘንድሮ መመዝገቢያን ጨምሮ 29 ሺሕ ብር በላይ መክፈል ይጠበቅበታል ነው ያሉት፤ ተማሪዎች።
ጭማሪው ከመጀመሪያ ጀምሮ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን እስከሚማሩ ኹሉም ተማሪዎች ላይ መሆኑን አንስተውም፣ ዩኒቨርሲቲው የመንግሥት ሆኖ ሳለ እንዲህ ዓይነት ያልተጠበቀ ጭማሪ ማድረግ ምክንያታዊ አይደለም ነው ያሉት።
የወቅቱን የኑሮ ውድነት ያላገናዘበ ክፍያ ተመን ነው ያሉት ተማሪዎች፣ የመንግሥት ተቋም በመሆኑም ማኅበራዊ ኃላፊነት ሊሰማው ይገባ ነበር ብለዋል። ተማሪዎች ጉዳዩን አስመልክቶ ከዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ ስንጠይቅ፣ ዩኒቨርሲቲው ወጭዎቹን መሸፈን ባለመቻሉ የተደረገ ጭማሬ ነው ተብለናል ነው ያሉት።
መልስ መስጠት የማይፈልጉ አካላትም መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ይሆናሉ መባሉን ተከትሎ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይህን ለማስጀመር ሊሆን ይችላል በእጥፍ የጨመረው ብለዋል።
ስለሆነም፣ በተለይ ለመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ ባልተጨመረበት ሁኔታ የትምህርት ክፍያው በእጥፍ መጨመሩ የመማር ፍላጎት ላላቸው ሰዎች በጣም ተስፋ አስቆራጭ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
የዩንቨርሲቲው የተማሪዎች ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ሠራተኛ (ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ) እንደተናገሩት፣ ለየኮሌጆች የዋጋ ጭማሪ መኖሩን እንጂ የተነገራቸው ለምን እንደተጨመረ የተገለጸ ነገር የለም ብለዋል። አክለውም፣ ክፍያዎች ላይ ከ60 እስከ 100 በመቶ ጭማሪ መደረጉን አንስተው፣ የመመዝገቢያ እና የኮርስ ክፍያዎች ግን በእጥፍ ነው የዋጋ ጭማሬ የተደረገባቸው ሲሉ ተደምጠዋል።
በዚህም የመግቢያ ፈተና አልፈው በዚያው የቀሩ ብዙ ተማሪዎች መኖራቸውን አውቃለሁ ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ከዩኒቨርሲቲው ሕዝብ ግንኙነት ክፍል እንዲሁም ከአካዳሚክስ ምክትል ፕሬዝዳንት ቢሮ ምላሽ ብትጠይቅም አናውቅም ያሉ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጣሰው ወልደሃና (ፕ/ር) ደግሞ ‹‹ከቢሮ ውጭ ነኝ በዚህ ሳምንት አይመቸኝም›› በማለታቸው ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም።
የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ክፍያ ሥርዓት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የመመልከት ሥልጣን እንደሌለው ገልጿል።
ይሁን እንጂ ተማሪዎች ከገንዘብ ጉዳይ ጋር በተገናኘ መብታቸውን የሚያስከብርላቸው ጠንካራ ተቋም ባለመኖሩም፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብዝበዛ እያደረሱባቸው መሆኑን ተቋሙ ሳይጠቅስ አላለፈም።
ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015



