በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያውያን ቀን በመጪው ህዳር 10 ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

0
705

ረቡዕ ጥቅምት 30 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያውያን ቀን በመጪው ህዳር 10 ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሚኖሩባቸው አገራት አንዷ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ናት።

ኢትዮጵያውያኑም በየዓመቱ በአቡዳቢና ዱባይ አብሮነታቸውን የሚያጠናክሩበትን የኢትዮጵያውያን ቀንን የሚያከብሩ ሲሆን፣ ዘንድሮም በመጪው ህዳር 10፣ 2015 በደመቀ ኹኔታ ለማክበር ዝግጅት እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ቀኑ በተለያዩ መርኃ ግብሮች የሚከበር ሲሆን፣ ባህላዊና የተለያዩ ኪናዊ ኹነቶችን ጨምሮ በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳይ ላይም ምክክር እንደሚደረግም ታውቋል።

ዝግጁቱን አስመልክቶ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ እንዳሉት፤ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ መልኮች አገራቸውን እያገዙ ነው።በተለይም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታና ባለፉት ኹለት ዓመታት በመንግስት ለቀረቡ አገራዊ ጥሪዎች ምላሽ በመስጠት ረገድ የላቀ እገዛ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የዘንድሮው የኢትዮጵያውያን ቀን ጦርነት ቆሞ የሰላም ሥምምነት በተፈረመበት ሰሞን የሚካሄድ መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደር ሱሌማን፣ በዓሉ ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያኑ ለአገር መልሶ ግንባታ በሚኖራቸው ቀጣይ አስተዋፅኦ ላይ የሚመከርበት እንደሆነም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያውያኑ እንደ ቀደመው ጊዜ ኹሉ በቀጣይም ባካበቱት እውቀትና ባላቸው ሀብት አገራቸውን እንዲያለሙ ለማድረግ ኤምባሲው እየሰራ እንደሆነ አስታውሰው፣ በአገር ውስጥም ያለውን ኹኔታ ማመቻቸትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዘበዋል።

ዘንድሮ በሚካሄደው የኢትዮጵያውያን ቀን ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here