በመንግሥት እና በህወሓት መካከል የሚካሄደው ንግግር እስከ አርብ እንደሚቀጥል ተነገረ

0
719

ረቡዕ ጥቅምት 30 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት ባለፈው ሳምንት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሰላም ሥምምነት ከተፈራረሙ በሗላ በናይሮቢ የቀጠለው ንግግር እስከ አርብ ሊቆይ እንደሚችል ተነገረ።

የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ ሰኞ ጥቅምት 28/2015 በኹለቱም ወገኖች ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች አማካይነት መካሄድ የጀመረው ንግግር ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 30/2015 ይጠናቀቃል ተብሎ ሲጠበቅ ነበር።በኬንያ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት እንደተናገሩት በኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና በህወሓት ተወካዮች መካከል እየተካሄደ ያለው ንግግር እስከ አርብ ሕዳር 03/2015 ድረስ ይቀጥላል።

በተጨማሪም በኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ያሉ ምንጮች ንግግሩ ዛሬ ረቡዕ እንደማይጠናቀቅ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

እየተካሄደ ያለው ንግግር በተያዘለት ጊዜ ረቡዕ ሊያበቃ የሚችልበት ዕድል ጠባብ በመሆኑ ኹለት ቀናትን ጨምሮ እስከ አርብ ሊቀጥል እንደሚችል ቢቢሲ ከዲፕሎማቱ ለመረዳት መቻሉን ዘግቧል።

ኬንያ ናይሮቢ ውስጥ በኹለቱ ወገኖች ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች መካከል እየተካሄደ ያለው ንግግር በዝግ እየተደረገ ሲሆን፤ እስካሁን ስላለው ሂደትና ስለደረሱበት ውጤት የተባለ ነገር የለም።ውይይቱ ወደሚካሄድበት የናይሮቢ፣ ካረን ሞራን ማዕከል ከኹለቱ ወገኖች እና ከአሸማጋዮች በስተቀር መግባት የማይቻል ሲሆን፣ በንግግሩ ማጠቃለያ ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here