ሕገ ወጥ የትንባሆ ንግድን መቆጣጠር የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱ ተሰማ

0
871

ሕገ ወጥ የትንባሆ ንግድን መቆጣጠር የሚያስቸል ረቂቅ አዋጅ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንዳዘጋጀ  የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አስታወቀ።

ረቂቅ አዋጁ የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ2018 ሕገ ወጥ የትምባሆ ምርቶችን ለመቆጣጠር ያወጣውን ፕሮቶኮል ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን፣ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ቁጥጥር የሚደረግባቸው ምርቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አስናቀች ዓለሙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ረቂቅ አዋጁ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደቀረበ የገለጹት አስናቀች፣ በኢትዮጵያ ያለውን ሕገ ወጥ የትምባሆ ንግድ ለመቆጣጠር ያስችላል ተብሏል። በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ በጉምሩክ ኮሚሽን፣ በምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን እንዲሁም በጸጥታ አካላት ትብብር ለሚሠሩት የመቆጣጠር ሥራዎች አመቺነትን የሚፈጥር እንደሆነ ተነግሯል።

ረቂቅ አዋጁ ከጸደቀ በኋላም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ለመሥራት ስምምነቶች እንዳሉ የተናገሩ ሲሆን፣ ረቂቅ አዋጁን ለምክር ቤቱ በማቅረብ ሂደት ውስጥ በርካታ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ሌሎች ተቋማት ጋር ሰፊ ውይይቶች መካሄዳቸው አዋጁን ተግባራዊ በማድረጉ ሂደት ውስጥ መልካም አጋጣሚዎችን እንደሚፈጥርም ተገልጿል።

ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ 199 ሚሊዮን 245 ሺሕ ብር የሚያወጣ በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ የትምባሆ ምርት ባለሥልጣኑ በተሳተፈባቸው የቁጥጥር ሥራዎች መያዝ መቻሉን የተናገሩት አስናቀች፣ በጉምሩክ ኮሚሽን እንዲሁም በጸጥታ አካላት ቁጥጥር የተያዘ ተጨማሪ ሕገ ወጥ የትምባሆ ምርትም እንደሚኖር ገልጸዋል።

አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ የንግድ ተቋማት ውስጥም ባለፉት ሦስት ወራት ወስጥ በተደረጉ ድንገተኛ ፍተሻዎች 3.2 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ያልተፈቀደላቸውና በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የገቡ የትንባሆ ምርቶችን መያዝ መቻላቸውንም አስናቀች ተናግረዋል።

እንዲህ ዓይነቱን ሕገ ወጥ የትንባሆ ምርቶች ዝውውርን ለመቆጣጠር ከሕግ ማዕቀፎች ባለፈ የተቋማትንና የኅብረተሰቡን ትብብር እንደሚጠይቅ የገለጹት አስናቀች፣ በትብብር መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ከሕገ ወጥ ንግድ ቁጥጥር በተጨማሪ የትንባሆ ምርቶችን መጠቀም በተከለከለባቸው ቦታዎችም የሚጠቀሙ ሰዎች እንዳይኖሩ አዋጅና መመሪያዎችን ማስፈጸም የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ባለሥልጣኑ ባለፉት ሦስት ወራት በአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ እንዲሁም ሀረሪ ክልሎች ኅብረተሰቡን የማስተማርና አዋጅና መመሪያዎች እንዲከበሩ የማድረግ የዘመቻ ሥራዎችን ከተባባሪ አካላት ጋር እንደሠራ ተጠቁሟል።

በገለልተኛ የጥናት ቡድኖች ከዚህ በፊት በተደረጉ ጥናቶች በኢትዮጵያ የሕገ ወጥ የትምባሆ ንግድ ድርሻ 32 በመቶ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ባለሥልጣኑ የቁጥጥር ሥራውን ከመሥራት ባለፈ እንዲህ ዓይነት የጥናት ሥራዎችን መሥራት እንደማይችል ተነግሯል።

ይሁንና በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የትንባሆ ምርት አምራች ድርጅቶች እንዲህ ዓይነቱን የሕገ ወጥ ንግድ ድርሻ ከፍተኛ ነው በማለት ራሳቸውን የማስተዋወቅና ተቀባይነታቸውን የማጠናከር ሥራ መሥራት የተለመደ እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሯ፣ በገለልተኛ ወገን የገበያው ሁኔታ እንደሚጠና ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ያለው አንድ የትምባሆ አምራች ድርጅት እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሯ፣ ምርቶቹን ማስተዋወቅ እንደማይችል ገልጸው፣ ምርቶቹን በሚሸፍንባቸው መሸፈኛዎች ላይ የትንባሆን ጎጂነት የሚያሳውቁ ማስታወቂያዎች በየኹለት ዓመቱ እየተቀያየሩ የሚቀርቡ ሲሆን፣ በቀጣይ ወራትም አዲስ ማስታወቂያዎች ይፋ እንደሚደረጉ ተናግረዋል።

የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በ2010 ይፋ ባደረገው የጎልማሶች የትምባሆ ተጠቃሚነት ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ ከ3.4 ሚሊዮን በላይ የትንባሆ አጫሾች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ 2.2 ሚሊዮን የሚሆኑት የትንባሆ ምርቶችን በየቀኑ የሚጠቀሙ ናቸው።

አንድ መደበኛ አጫሽ በአንድ ቀን በአማካይ 10 ፍሬ በፋብሪካ የተመረቱ ሲጋራዎችን እንደሚያጨስ ማስታወቁ ይታወሳል።


ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here