ከሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ጥገኝነት የመላቀቅ ተስፋ

0
1547

አርሶ አደር ረኢስ ጀማል በጅማ ዞን ዴዶ ወረዳ የኢላላ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ብዙዎቹን ማሳዎቻቸውን ከማዳበርያ ጥገኝነት ነጻ ካወጡ ሦስት ዓመታትን ማስቆጠራቸውን ይናገራሉ። ከሦስት ዓመት በፊት ለማዳበርያ ያወጡት የነበረውን ወጪ በሦስት እጅ መቀነስ ችለዋል።

ረኢስ በማሳዎቻቸው ገብስ፣ ስንዴ፣ ድንች እና ፖም ያመርታሉ። ለእነዚህ ሁሉ ሰብሎች “ቨርሚ ኮምፖስት” በተባለ ቴክኖሎጂ በራሳቸው በግቢያቸው የሚያመርቱትን የተፈጥሮ ማዳበርያ እየተጠቀሙ ነው። ታድያ የማዳበርያ ወጪ መቀነስ ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉም የምርት ዓይነቶች ቀድሞ ከሚያገኙት ዕጥፍ በላይ ምርት እያገኙ መሆናቸውንም ይናገራሉ። ሙሉ በሙሉ የማዳበርያ ወጪያቸውን ለማስቀረት ግን ቨርሚ ኮምፖስት የተባለውን የተፈጥሮ ማዳበርያ በብዛት የማምረት ችግር ገጥሟቸዋል።

የኢትዮጵያ መሬት እየታረሰ ለብዙ ሺሕ ዓመታት ምርት ሲሰጥ ኖሯል። በውጪ አገራት በፋብሪካ ተመርቶ የሚመጣን ማዳበርያ መጠቀም ከተጀመረ ግን 50 ዓመት አልሞላም። ታድያ የማዳበርያ ፍጆታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ከመምጣቱም ባሻገር፣ የማዳበርያው የጎንዮሽ ችግሮች የምርቱንም የመሬቱንም ዕጣ ፈንታ አሳሳቢ አድርጎታል።

በዘርፉ የተደረጉ ጥናትና ምርምሮች እንደሚያሳዩት ከማዳበርያ ጥገኝነት መላቀቅ ይቻላል። በተግባር ተሞክረው በታዩ በአርሶ አደሩ ቀዬ ከሚገኙ ግብዓቶች መመረት የሚችሉ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ተፍጥሯዊ ግብዓቶች ሙሉ በሙሉ ሰው ሠራሽ ማዳበርያን መተካት እንደሚቻል ባለሙያዎችም ተጠቃሚዎችም ይናገራሉ። ታድያ ለዚህ የሚያስፈልገው እና እስካሁን የጎደለንም ጉዳዩን የተረዳ ቆራጥ የፖለቲካ አመራር ነውም ይላሉ።

ፒ ኤች ኢ ኢትዮጵያ የተባለ ግብረ ሠናይ ድርጅት በጅማ ዞን ዴዶ ወረዳ ኹለት ቀበሌዎች ላይ በዚህ ጉዳይ ላይ የማሳያ (ፓይለት) ፕሮጀክት እያካሔደ ዓመታትን አስቆጥሯል። እነ አርሶ አደር ረኢስ በዚህ ፕሮጀክት ታቅፈው ውጤታማ ከሆኑት መካከል ናቸው።

የፒ ኤች ኢ ኢትዮጵያ የሥነ-ሕዝብ እና የኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራሞች አስተባባሪ አሕመድ መሐመድ እንደሚሉት፣ ድርጅታቸው ሥፍራውን ሲመርጠው በግብርናው ዘርፍ አካባቢውን የገጠሙትን ተግዳሮቶች እና ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ብዛትን ታሳቢ በማድረግ ነው።

የኅብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል የተቀናጁ ፕሮጀክቶችን ይዘው የመጡ ሲሆን ጤና፣ ግብርና፣ የፋይናንስ አቅርቦት እና የአካባቢ ጥበቃ ሥራን አጣምረው መምጣታቸውን ይናገራሉ። የአካባቢው አፈር ለምነት እየቀነሰ በመሔዱና አሲዳማነት ያለው በመሆኑ ቀድሞ በአካባቢው ይበቅሉ የነበሩት እንደ ቀርከሀ፣ ነጭ ሸንኩርት እና መሰል ምርቶች ጠፍተዋል። የገብስ ምርት በአካባቢው በስፋት የሚበቅል ቢሆንም፣ እሱን በተደጋጋሚ በበሽታ እና በዋግ የመጠቃት ችግር አጋጥሞታል። በመሆኑም ኅብረተሰቡ የአካባቢውን ደን ወደመጠቀም ፊቱን ማዞሩ አካባቢው እየተራቆተ እንዲሔድ አድርጓል።

እነዚህን ሁኔታዎች ለመቀየር ተመጋጋቢ ፕሮጀክቶች የተነደፉ ሲሆን የቤተሰብ ምጣኔን፣ መነሻ ፋይናንስ በማቅረብ ብድርና ቁጠባን፣ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን በማኅበር ተደራጅተው አምርቶ መሸጥን እና መሰል ፕሮጀክቶችን አስጀምሯል። ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ዐቢይ የሆነው የተፈጥሮ ማዳበርያን በቀያቸው የማምረትና መጠቀም ሒደት አንዱ ነው። በዚህ ፕሮጀክት ከአካባቢው ተሰደው የነበሩ ተክሎች ዳግም ከአካባቢው ጋር ታርቀው፣ በቅለው ፍሬ መስጠት ችለዋል።

አሁን እነ ረኢስ ውጤታማ የሆኑበት የተፈጥሮ ማዳበርያ የሚመረተው ከከብቶች እዳሪና ከማናቸውም ሊበሰብሱ ከሚችሉ ቆሻሻዎች ጭምር ነው። በዚህ ውስጥ የእህል ገለባና ብዕር፣ የዛፎች ቅጠል፣ የምግብ ትርፍራፊ ሁሉ ይካተታል። እነዚህን ግብዓቶች ወደ ማዳበርያነት የሚቀይረው ደግሞ ትል ነው። በተለምዶ የተስቦ ትል ወይም ቀይ ትል ይባላል። በአብዛኛው የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይ በክረምት ወቅት ብስባሽ ባለበት አካባቢ የሚታይ፣ በሰውና እንስሳት ላይም ሆነ በአካባቢ ላይ ጉዳት የማያስከትል ፍጥረት ነው።

ማዳበርያ እጅግ በተወደደብን ሰዓት ነው ዘዴው የደረሰን የሚሉት አርሶ አደር ረኢስ፣ በግቢያቸው የሚያመርቱት ማዳበርያ ቢበዛ ኹለት ወር ነው የሚፈጀው በማለት ስለ ምርት ሒደቱ ያብራራሉ። ከግብረ ሠናይ ድርጅቱ ትሉን ከወሰዱ በኋላ በአርሶ አደሮች ማሠልጠኛ ማዕከል ባዩት መሠረት ወትሮ እየተጣለ ቦታ ያጣብብ የነበረውን የከብቶች እዳሪ ከእንጨት በሚሠራ ማጠራቀሚያ ውስጥ በማስገባት ትሉን እዛ ውስጥ ይጨምሩታል። በየተወሰነ ጊዜም ውኃ ይጨምሩበታል።

ትሉ በፍጥነት እየተራባ በማጠራቀሚያው ውስጥ የተሞላውን የከብቶች ፍግ እና የተለያዩ ቅጠላ ቅጠሎችን በፍጥነት በመብላት ያበሰብሳል። ትሉ በራሱ ጊዜ በአንድ ጎን በልቶ ሲያበቃ ወዳልተበላው ስፍራ ይዛመታል። ይሄኔ የተበላውን ወስዶ በማሳቸው ላይ መበተን የነ ረኢስ ሥራ ነው። በዚህ መልኩ አንድ ጊዜ ያዳረሱትን ማሳ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ያለ ምንም ተጨማሪ ማዳበርያ ማረስ እንደሚያስችላቸው አርሶ አደር ረኢስ ይናገራሉ።

የአርሶ አደር ረኢስን ሐሳብ የሚጋሩትና በዴዶ ወረዳ ሶላ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አብዶ ናስር እሳቸውና ዘመዶቻቸውም በቨርሚ ኮምፖስት/ማዳበርያ መጠቀም እንደጀመሩ ይናገራሉ። ማዳበርያውን ከማምረትም አልፈው አበስባሽ ትሉን ለሌሎች አርሶ አደሮች መሸጥ መጀመራቸውንም ይናገራሉ።

አብዶ ናስር እንደሚሉት ይህንን ብልሃት መጀመርያ ሲሰሙ ብዙም አላመኑበትም ነበር። የመጀመርያው ዓመት ካለፋቸው በኋላ ግን ከ2012 ጀምሮ በጓሮ አትክልቶች ጀምረው ተጠቅመዋል። ከ2013 ጀምሮ አብዛኛውን እርሻቸውን በዚሁ ማዳበርያ መሸፈን ችለዋል። ይህን በማድረጋቸውም ከማሳቸው ከወትሮው እጥፍ ምርት ማግኘታቸውንም ይናገራሉ። ስላለፈው ጊዜ የሚቆጩት አርሶ አደር አብዶ፣ አሁንም ማሳዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ በዚህ ተፈጥሯዊ ማዳበርያ ለመሸፈን ችግራቸው ብዛት ማምረት መቻል ላይ ነው።

አርሶ አደሮቹ እንደሚሉት አንድ ሔክታር መሬት በዚህ ማዳበርያ ለማዳረስ እስከ 80 ኩንታል ያስፈልጋቸዋል። አንድ ጊዜ በሳጥናቸው ሞልተው የሚያመርቱት ማዳበርያ እስከ ኹለት ወር የሚቆይ ሲሆን፣ ከማምረቻዎቻቸው አነስተኛነት አንጻር ለሁሉም ማሳዎቻቸው የሚበቃ ማዳበርያ ለማግኘት እንደተቸገሩ ይናገራሉ።

ለዚህ አብዶ ናስር፣ ‹‹የአንድ አካባቢ አርሶ አደሮች በጋራ ሆኖን የተሻለ መሥርያ ቦታ በመሥራት ብዛት ማምረት ላይ ብንሠራ፣ ወይም መንግሥት ማዳበርያ ከውጪ ከሚያስገባልን ይሄንን አምርቶ ቢሸጥልን ጥሩ ነበር›› ይላሉ።

በዚህ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ውጤቱን ማየት የቻሉት በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን አቅራቢያ ያለችው የፍቼ አርሶ አደሮችም ስለ ተሞክሮአቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አርሶ አደሮቹ በማዳበርያው ምርታማነት እና ጥቅሞች የሚስማሙ ሲሆን በማዳበርያው ሲጠቀሙ ግን አረም የሚበዛ መሆኑን ይናገራሉ።

እነዚህን የአርሶ አደሮቹን አስተያየቶች አዲስ ማለዳ ለባለሙያ አቅርባለች። በዚህ የቨርሚ ኮምፖስት ተፈጥሯዊ ማዳበርያ ላይ ምርምሮችን በመሥራት የሚታወቁት እና በጅማ ግብርና ምርምር ማእከል ተመራማሪ የሆኑት ረሺድ አባ ፊጣ (ፒ ኤች ዲ) ይህን የቨርሚ ኮምፖስት ተፈጥሯዊ ማዳበርያን በመጠቀም አገሪቱን ሙሉ በሙሉ ከሰው ሠራሽ ማዳበርያ ጥገኝነት ማላቀቅ ይቻላል ይላሉ።

አርሶ አደሮቹ ያነሷቸው ጉዳዮች በተናጥል በባለሙያ መታየት አለባቸው የሚሉት ረሺድ፣ ፕሮጀክቱን በትክክል የተረዳ ባለሙያና አመራር በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩ የሚመጡ ጉድለቶች ፕሮጀክቱን በትክክል እንዳይተገበር ከማድረጉም በላይ አርሶ አደሮች በተዛባ መልኩ እንዲረዱት ሊያደርግ ይችላል ይላሉ።

እንደሳቸው አገላለጽ፣ የአተገባበር ችግር ካልሆነ አንድ ሔክታር መሬት እስከ 80 ኩንታል የሚጠይቅ አይደለም። ለሁሉም መሬቶችም ተመሳሳይ መጠን አይደረግም ይላሉ። ይልቁንም በአካባቢው ግብርና ቢሮዎች በኩል አፈሩ እየተጠና በልክ በልኩ መስጠት እና እንዲያውም በየዓመቱም የማዳበርያውን መጠን እየቀነሱ መሔድ ያስፈልጋል ይላሉ።

ያን ያህል መጠን የሚወስድም ቢሆን ሰው ሠራሽ ማዳበርያን ከመግዛት እጅግ ይሻላል ባይ ናቸው። የአረሙን ጉዳይ በተመለከተ መሬት እጅግ ለም ሲሆን እንደሱ ነው ያሉ ሲሆን፣ ለዚህም ቢሆን መላ አይጠፋውም ባይ ናቸው። በአንድ በኩል ወትሮም አረም በእጅ የሚታረም አልያም መድኃኒት የሚደረግበት በመሆኑ ለዚህኛውም ያንኑ መጠቀም ይቻላል። በመስመር መዝራትና ሌሎች አማራጮችም ይኖሩታል፣ ዋናው ነገር በባለሙያ መታገዙ ላይ ነው ይላሉ።

ረሺድ እንደሚሉት፣ የቨርሚ ኮምፖስት ማዳበርያ ግብዓቱ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በገጠርም ሆነ በከተማ የሚገኝ ነው። ከከብቶች እዳሪ በተጨማሪ በጥናት የተለዩ በርካታ ዓይነት የትም ሊገኙ የሚችሉ ግብዓቶች አሉ። ከሰው ሠራሽ ማዳበርያ አንጻርም ይኼኛው በርካታ ብልጫዎች እንዳሉት ይናገራሉ።

በዋናነት የቨርሚ ኮምፖስት ማዳበርያ ከሰው ሠራሽ ማዳበርያ አንጻር ያለው ብልጫ እህሉን ለሚመገበው ሰውም ሆነ ለአፈሩ የጎንዮሽ ጉዳት አልባ መሆኑ አንዱ ሲሆን፣ ሰው ሠራሽ ማዳበርያ ግን በሳይንስ የተረጋገጡ በርካታ የጤና ጉዳቶችን ያስከትላል። የአፈር ለምነትንም የበለጠ እየቀነሰ የማዳበርያ ጥገኛ ያደርጋል። ለአፈር ለምነትና ከባቢ አየር አስፈላጊ የሆኑ ነፍሳትን ይገድላል፣ እየታጠበ ወደ ወንዝ ስለሚገባም ውኃን በመበከልም በሰውና እንስሳት ጤናና መራባት ላይ ጉዳት ያስከትላል።

ጉዳቱ ከዚህም በላይ ብዙ ነው ያሉት ረሺድ ከዚህ የተነሳ እንደ አገራችን የማዳበርያ አቅርቦት ችግር የሌለባቸው፣ ማዳበርያን የሚያመርቱ እንደ አሜሪካና ሕንድ ያሉ አገራት ሳይቀሩ ሰው ሠራሽ ማዳበርያ መጠቀምን ለአርሶ አደሮቻቸው አያበረታቱም፤ ይልቁን በዚህና ሌሎችም ዓይነት በኛም አገር ሊተገበሩ የሚችሉ መሰል የባዮሎጂካል ቴክኖሎጂ ተፈጥሯዊ ማዳበርያን እየተጠቀሙ ነው ይላሉ። የአገራችን የግብርና ምርት በዓለም ዐቀፉ ገበያ ተቀባይነት የሚኖረውም፣ ከሰው ሠራሽ ማዳበርያ ውጪ ሲመረት ነው በማለት ለአብነትም የኢትዮጵያ ቡና ተፈላጊነት ዋናው ምክንያት ‹ኦርጋኒክ› (ተፈጥሮአዊ) ወይንም ያለ ማዳበርያ የተመረተ መሆኑ ነው ይላሉ።

የኢትዮጵያ መሬት ሰው ሠራሽ ማዳበርያ መጠቀም የጀመረው ከደርግ ዘመን ወዲህ ነው የሚሉት ረሺድ፣ ቀደሞ ለአፈር ለምነት ችግር የተጋለጠው የሰሜኑ የአገራችን ክፍል ሲሆን፣ በሒደት ደግሞ ሌሎችም ማዳበርያን ወደ መጠቀም መጥተዋል። የደቡባዊው ኢትዮጵያ ምድር አሁንም ድረስ ማዳበርያ መጠቀም ሳያስፈልገው መሬቱ በቂ ምርት የሚሰጥ በርካታ አካባቢዎች አሉት ሲሉ ይናገራሉ።

ከዓለም ዐቀፍ የልማት አጋሮች በኩል ማዳበርያን እንድንጠቀምና በመጠቀምም እንድንቀጥል የሚደረጉ ግፊቶች ይታያሉ ያሉት ባለሙያው፣ በአንድ በኩል በረሀብ ታልቃላችሁ በማለት ሲሆን በሌላ በኩል ግን ፋብሪካዎቻቸው የኛ ገበያ ስለሚያስፈልጋቸው ይመስላል ይላሉ።

ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከፍተኛ የሆነ የውጪ ምንዛሪ ለማዳበርያ ግዢ ታውላለች። ከገንዘብ የመግዛት አቅም እና ሌሎች ዓለም ዐቀፍ ሁኔታዎች ላይ ተመርኩዞም የግዢ ዋጋውም በየዓመቱ ሲጨምር ይስተዋላል። ለ2014 የምርት ዘመን ማዳበርያ ለመግዛት እንኳ ዋጋው 150 በመቶ ያህል ጨምሮ 12.8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበርያ ለመግዛት ኢትዮጵያ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማድረጓን መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ አኃዝ ዋጋው ከመወደዱ የተነሳ ሊገዛ ከነበረው ማዳበርያ በሚሊዮን ኩንታል የሚቆጠረው ቀርቶ ማለት ነው።

ከዚህ የገንዘብ ወጪ ባሻገር እንዲህም ተገዝቶ ከሰው ሠራሽ ማዳበርያ ውስጥ ማሳው ላይ የሚዘራው እህል የሚጠቀመው 20 በመቶውን ብቻ መሆኑን ተመራማሪው ይናገራሉ። የተቀረው አፈር ውስጥ የሚቀር ነው። በሌላ አነጋገር አርሶ አደሩ ማሳው ላይ ከሚጠቀመው 100 ኪሎ ግራም ማዳበርያ ውስጥ ለእህሉ ጥቅም የሚውለው 20 ኪሎ ግራም ብቻ ነው ማለት ነው።

ይህን ችግር ለመቅረፍም በቨርሚ ኮምፖስት የተመረተውን ማዳበርያ ከሰው ሠራሹ ጋር አደባልቀው፣ ግማሽ በግማሽ አድርገው ሲጠቀሙ የእህሉን ማዳበርያ የመጠቀም ውጤታማነት በመጨመር ማዳበርያ መቆጠብም ያስችላል ይላሉ።

እንደ ረሺድ አስተያየት፣ ማዳበርያን መጠቀም ቢቸግር ነው እንጂ የሚመከር መላ አይደለም። ከዚህ ለመላቀቅም ቨርሚ ኮምፖስቱን ጨምሮ በአገራችን በሚገባ መተግበር የሚችሉ፣ ማዳበርያን ከመግዛትም ሆነ ከማምረት ባነሰ ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት መመረት የሚችሉ ተፈጥሯዊ በሆኑ የቴክኖሎጂ አማራጮች የሚቀርቡ ማዳበርያዎች አሉ። ዋናው ችግር የዘርፉን አንገብጋቢነት የተረዳ ቆራጥ አመራር አለመኖሩ ነው።

በተወሰነ መልኩ በተሠሩ ሥራዎች ጉዳዩን ለፖለቲካ ፍጆታ በማዋልና ለባለሙያ ቅድሚያ ባለመስጠት በአግባቡ ሳይተገበር እየቀረ ቴክኖሎጂው ችግር ያለበት እንዲመስል እየሆነ ነው ይላሉ ረሺድ። ይህን በማስቀረት፣ ለባለሙያ ቅድሚያ ተሰጥቶ፣ ሒደቶቹ በትክክል ቢተገበሩ በተለይ የቨርሚ ኮምፖስት ማዳበርያ አመራረት አርሶ አደራችንን በቀላሉ ከማዳበርያ ጥገኝነት በማላቀቅ ውጤታማ የግብርና ሴክተር እንዲኖረን ያደርጋል ይላሉ።


ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here