ሌብነት ተባብሷል ተብሏል
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የወቅቱን ዋጋ ንረት መቆጣጠር እንዳልቻለ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር የ2015 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ውይይት ባደረገበት ወቅት፣ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተጣለበትን የመንግሥትን ሥራ የማስፈጸም ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ አይደለም የሚል ትችት አቅርቧል።
ቋሚ ኮሚቴው ሕዝቡ ትዕግስት ባጣ መልኩ እየጮኸ መሆኑን በማንሳት፣ ለማኅበረሰቡ የማያዝኑ ነጋዴዎችም እንደፈለጉ እየበዘበዙት ነው ብሏል። ማኅበረሰቡን ወደ ታች ወርደን ስንጠይቅ ዘይትና ስኳር አለ ወይ? እስከማለት ደርሷል ያሉት የቋሚ ኮሚቴው አባላት፣ አገራችን የነበረችበት ሁኔታና ዓለም ዐቀፋዊ ችግሮች ቢኖሩም ግን እስከመቼ ነው እነዚህን እንደምክንያት እያነሳን ሌብነትና ብልሹ አሠራርን መቆጣጠር የማንችለው? ሲሉም ጠይቀዋል።
ሕዝቡ የዋጋ ንረቱ መስተካከል ያልቻለው ከታች እስከ ፌዴራል ያሉ የመንግሥት አመራሮች በሕገ ወጥ ንግድ ውስጥ በመሰማራታቸው ነው ብሎ እንደሚያምን የቋሚ ኮሚቴ አባላት ጠቁመዋል። ከዚህ አንጻር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሩብ ዓመት ሪፖርቱ ይፋ ያደረገው ነገር ባለመኖሩ ወቀሳ ቀርቦበታል።
የዋጋ ንረቱን ለማስተካከል የሚቀርቡ መፍትሔዎች ለውጥ ካላመጡስ ለምንድን ነው ሌላ ስር ነቀል ለውጥ የሚያመጣ መፍትሔ ማግኘት ያልተቻለው? ሲሉም አባላቱ ጠይቀዋል። ብዙ የመንግሥት አካላት ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ ሊሆን ይችላል ያለው ቋሚ ኮሚቴው፣ ሆኖም ግን መሬት ላይ ያለው ‹የሕዝብ ጩኸት› የሚደመጠውና መልስ የሚሰጠው መቼ ነው በማለት ጥያቄውን አቅርቧል።
የበፊቱ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኹለት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሆኖ የተዋቀረው፣ ይህን ትልቅ ችግር ይፈታል ተብሎ መሆኑን ያስታወሰው ቋሚ ኮሚቴው፣ ችግሩን መፍታት ካልቻለ የተጣለበትን ኃላፊነት እየተወጣ እንዳልሆነ ይወሰዳል ሲልም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ኮንኗል።
ቋሚ ኮሚቴው ከፍተኛ እሮሮ ከሚቀርብባቸው ተቋማት መካከል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አንዱ መሆኑን ጠቅሷል። ሕዝብ የሚፈልገው ንግግር ሳይሆን መፍትሔ በመሆኑ ገበያውን ለማረጋጋት ለውጥ የሚያመጡ እርምጃዎችን እንዲወስድ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለቋሚ ኮሚቴው የላከውን የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት በተመለከተም፣ የቁጥር መጣረስ ያለበት ነው የተባለ ሲሆን፣ ዓመታዊ ዕቅዱም የትኩረት አቅጣጫዎችን የሳተ እና በስሩ ካሉ ተጠሪ ተቋማት ያነሰ የዕቅድ አዘገጃጀት ያለው ነው ሲሉ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ትችት ሰንዝረዋል።
እንዲሁም፣ የተሰጠውን ግብረመልስ በቀጣይ ሪፖርት ላይ የማያካትት፣ ማስተካከያ የማያደርግ እና ባላየ የሚያልፍ ተብሎ በተመሳሳይ ከተገመገሙ ተቋማት አንዱ ነው ያሉት አባላቱ፣ ይህም የሕዝብን ድምጽ ችላ እንደማለት ይቆጠራል ነው ያሉት።
መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት በዚሁ ተቋም ሥራ መሆኑን የጠቆመው ቋሚ ኮሚቴው፣ የተረጋጋ ገበያ ለመፍጠር ጠንካራ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ አሳስቧል።
ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከምክር ቤቱ የቀረቡት ሕዝብን የሚወክሉ አስተያየቶች ተገቢ ናቸው ያለ ሲሆን፣ ነገር ግን የአገሪቱን የማምረት አቅምና ዓለም ዐቀፍ ቀውስ መረዳት ያስፈልጋል ብሏል።
አንድ መሥሪያ ቤት ብቻውን የዋጋ ንረቱን መቆጣጠር እንደማይችል የጠቀሰ ሲሆን፣ ሌብነትና ብልሹ አሠራር እየተወሳሰበ መጥቷል ብሏል። ይህን ለማስተካከል ተብሎ የሚወጡ መመሪያዎች ሳይቀር የሌብነት ስልቱን እያወሳሰቡት ነው ብሏል።
በሩብ ዓመቱ ሊሰራጭ ከታቀደው ስኳር 34 በመቶ ብቻ መሰራጨቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ስኳር ኮርፖሬሽን ማቅረብ የሚገባውን መጠን ማቅረብ ባለመቻሉ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ሆኗል ተብሏል። ሲሚንቶን በተመለከተም ሕጋዊ አከፋፋይ ተብለው የተመረጡ አካላት ሳይቀር አሳፋሪ ተግባር ውስጥ ተሰማርተው እንደሚገኙ ተጠቅሷል።
ቋሚ ኮሚቴው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀራርቦ የመሥራት ክፍተት አለ ቢልም፣ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ግማሽ ጊዜዬን የማጠፋው ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየትና አብሮ በመሥራት ነው ብሏል።
ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015


