ማክሰኞ ኀዳር 6 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አጸደ ማሞ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “የኦነግ ሸኔ የትጥቅ ምንጭ ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሳይሰጡበት ቀርተዋል፡፡
የምክር ቤት አባሏ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ስለ “ኦነግ ሸኔ” የትጥቅ ምንጭ ያቀረቡት ጥያቄ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሳይሰጥበት ሰብሰባው ተጠናቋል፡፡
በመንግሥት በኩል “ኦነግ ሸኔ”ን በዜጎች ላይ ከሚያደርሰው ጥቃት ለማስቆም አመርቂ ሥራ አለመስራቱንም አባሏ አንስተዋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው መንግሥት “ኦነግ ሸኔ” ብሎ የሚጠራውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ኃይል፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ካሉ አካላት እገዛ እንደሚደርግለትም የምክር ቤት አባሏ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡ አባሏ አክለውም፤ ታጣቂ ቡድኑ በዜጎች ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት ለማስቆም የመንግሥትን ቁርጠኝነትና ዝግጅት እንዲያብራሩላቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፣ “ሸኔ ግን እንኳን ለኛ ለሚጋልቡትም ችግር ሆኗል፣ የማይጨበት የማይዳሰሰ፣ ፍላጎቱ የማይታወቅ” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ ተጣቂ ቡድኑን “ለሚጋልቡት” የተባሉትን አካላት ማንነት አልገለጹም፡፡ በሽብር የሚገኝ ነጻነትና ዴሞክራሲ የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሽብር መንገድ ዘላቂ ጥቀም ማምጣት አይቻልም ብለዋል፡፡
ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ተጣቂ ኃይል በኦሮሚያ ክልል በስፋት እየተነቀሳቀሰ የሚገኝ ታጣቂ ኃይል ሲሆን፣ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ማንነት መሰረት ያደረገ ጥቃት በንጹሐን ሰዎች ላይ እንደሚፈጽም የሰብዓዊ መብት ተቋማት ሳይቀሩ በተዳጋገሚ ሪፖርት ሲያቀርቡ ነበር፡፡
ታጣቂ ኃይሉ በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት ለማስቆም ችግሩ በሰላማዊ ውይይት እንዲፈታ ሀሳቦች እየቀረቡ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለውይይት ዝግጁ የሆነ ታጣቂ ኃይል ካለ መንግሥታቸው ለመነጋጋር ዝግጁ መሆኑን ለምክር ቤቱ ጠቁመዋል፡፡



