ረቡዕ ኀዳር 14 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት የሥራ ባልደረባ የሆነችው ጽዮን ተገኝ ትላንት ምሽት 12 ሰዓት አካባቢ አቅጣጫው ካልታወቀ ቦታ በተተኮሰ ጥይት ሕይወቷ ማለፉን የከተማ መስተዳድሩ አስታውቋል፡፡
ግለሰቧ ቤተሰብ ለመጠየቅ በባጃጅ ላይ እያለች በተተኮሰ ጥይት ህይወቷ ያለፈ ሲሆን፤ ግድያዉ ተጣርቶ ወንጀለኞችን በህግ ቁጥጥር ሥር ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ የሸዋሮቢት ከተማ አስተዳድር ባወጣዉ የሀዘን መግለጫ ተናግሯል።
ከተማ አስተዳደሩና መላው ሠራተኛ በጽዮ ህልፈተ ህይወት የተሰማዉን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ፤ ለወዳጅ ዘመዶቿ እንዲሁም ለቤተሰቦቿ መጽናናትን ለሟች ደግሞ ነፍሷን በአጸደ ገነት እንዲያኖርልን እንደመኛለን ብሏል፡፡
ስርዓተ ቀብሩም በዛሬዉ ዕለት 06 ቀበሌ ቆቦ ቃለ ህይወት ቅዱስ እግዚአብሄር አብ ቤተክርስቲያን ከቀኑ 7 ሰዓት እንደሚፈጸም ተነግሯል፡፡
በሸዋሮቢት ከዚህ ቀደም የከተማዋ ተቀዳሚ ከንቲባ የነበሩት ዉብሸት አያሌዉ በተመሳሳይ ጥቃት ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።



