ረቡዕ ሚያዚያ 25 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የዓለም ምግብ ፕሮግራም ያከማቸው የእርዳታ እህል ከተዘረፈ በኋላ ለትግራይ ክልል የሚያቀርበውን የሰብዓዊ እርዳታ ለጊዜው ማቋረጡን አስታውቋል፡፡
ተቋሙ የዕርዳታ ማከማቻ መጋዘኑ ስርቆት የተፈጸመበት መሆኑን ተከትሎ ጉዳዩ ተጣርቶ በማን እንደተዘረፈ እስከሚታወቅ ድረስ ለትግራይ ክልል የማቀርበው እርዳታ የለም ብሏል፡፡
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች በሚያገኘው ድጋፍ ለትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ ሲያደርስ ቆይቷል፡፡
የዕርዳታ ስርጭቱ ከሚያዚያ 12/2015 ጀምሮ መቆሙን ከተቋሙ ሠራተኞች መስማቱን ጠቅሶ አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል፡፡
ከመጋዘኑ የተሰረቀው የእርዳታ ምግብ በትንሹ 100 ሺሕ ሰዎችን ይመግብ ነበር የተባለ ሲሆን፤ በትግራይ ክልል ካለው ስድስት ሚሊዮን ገደማ አጠቃላይ ህዝብ አምስት ሚሊዮን የሚሆነው ህዝብ የእርዳታ ምግብ ፈላጊ መሆኑ ተመላክቷል፡፡



