300 ዓለም አቀፍ ተቋማት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ግልጽ ደብዳቤ ጻፉ

0
1085

በኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮ 24 ጊዜ የኢንተርኔት መቋረጥ መከሰቱ ተገልጿል

ረቡዕ ሚያዚያ 25 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) 300 ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የዘጋውን ኢንትርኔት አገልግሎት እንዲከፍት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን በግልጽ ደብዳቤ ጠይቀዋል፡፡

ተቋማቱ በጻፉት ደብዳቤ አገራት በቀውስ ጊዜ ቢሆን እንኳን የኢንትርኔት አገልግሎትን ከማቋረጥ መቆጠብ እንዳለባቸው ያሳሰቡ ሲሆን፤ በዚሁ መሰረት በኢትዮጵያ የተዘጋው የኢንትርኔት አገልግሎት መከፈት አለበት ብለዋል፡፡

ተቋማቱ በኢትዮጵያ የኢንተርኔት በመዘጋቱ በመንግሥት በኩል በተለይም አማራ እና ትግራይ ክልል የጦር መሳሪያ የመጠቀም አዝማሚያ መታየቱ እንደሚሳስባቸው የጠቆሙ ሲሆን፣ የኢንትርኔት አገልግሎት ሰብዓዊ መብቶችን ለማስጠበቅና በቀውስ ወቅት ድህንነትን ለማስጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢንትርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ ምክንያት ከሆኑ ምክንያቶች መካከል፤ ከልዩ ኃይል መልሶ ማዋቀር ጋር በተገናኘ በአማራ ክልል በመንግሥት ላይ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ አንዱ ነው ተብሏል፡፡ እንዲሁም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በፌደራል መንግሥት መካከል ተከስቶ የነበረው ውጥረት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የኢንትርኔት አገልግሎት ገደብ እንዲጣል ምክንያት መሆኑም ተመላክቷል።

በፖለቲካ አለመረጋጋት እና በተቋውሞዎች ምክንያት በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የኢንተርኔት አግልግሎት እንደሚቋረጥ የጠቆሙት ተቋማቱ፤ ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮ 24 ጊዜ የኢንተርኔት መቋረጥ መከሰቱን አስታውሰዋል፡፡

በግጭትና በቀውስ ወቅት ኢንትርኔት መዝጋት መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መሆኑን የተጠቀሰ ሲሆን፤ ዜጎች በችግር ጊዜ መረጃ የሚያገኙበትን ዕድል ማሳጣት አደገኛ ጥፋት ነው ብለውታል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ኢንትኔት አግልግሎት ገደብን የማንሳት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ግዴታ አለበትም ተብሏል፡፡

በመሆኑም መንግሥት የገደበውን የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲለቅና የማኅበራዊ ሚዲያን የመጠቀም ነጻነት የሚገደቡ የማኅበራዊ ሚዲያ ፕላትፎርሞች ላይ የተጣለውን የኢንትኔት አገልግሎት ገደብ እንዲያነሳ ተቋማቱ በደብዳቤያቸው አሳስበዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here