መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ በተደረገው ውይይት መግባባት ላይ አለመድረሱን አስታወቀ

0
793

ረቡዕ ሚያዚያ 25 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የፌደራሉ መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ባደረገው ውይይት መግባባት ላይ አለመድረሱን አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የሰሜኑ ጦርነት እንዲቆም አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እውቅና ለመስጠት በተዘጋጀው ሥነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ መንግሥታቸው ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ከሚያዚያ 17/2015 ጀምሮ የሰላም ድርድር እንደሚጀምር ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የኹለቱ ተደራዳሪ አካላት ተወካዮች ወደ ታንዛንያ በማቅናት ላለፉት 8 ቀናት ሲደራደሩ መቆየታቸው ይታወቃል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ በኦሮሚያ ክልል ያለውን ግጭት በማስወገድ ሰላምን ለማምጣት ያለመውና በታንዛኒያ ሲካሄድ የቆየው የሰላም ውይይት የመጀሪያ ምዕራፍ ዛሬ መጠናቀቁን አስታውቋል።

በመግለጫውም ውይይቱ በአብዛኛው በአዎንታዊ መልኩ የተከናወነ ቢሆንም በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ግን በዚህኛው የውይይት ምዕራፍ ስምምነት ላይ ለመድረስ አለመቻሉን ገልጿል።

ግጭቱን በዘላቂነትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስቆም እንዲቻል ኹለቱም አካላት የሰላም ውይይቱን መቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ላይ መግባባታቸውን ነው አገልግሎቱ ያስታወቀው።

“በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና እስካሁን ሲመራባቸው በነበሩ መሠረታዊ መርሖች መሠረት ግጭቱን በሰላማዊ መልኩ ለመፍታት መንግስት የጸና አቋም አለው።” ያለው መግለጫው ”ይህን መልካም አጋጣሚና በውይይት ችግሮችን የመፍታት በጎ ጅምር በመጠቀም ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለውን ፅኑ አቋም ዳግም ያረጋግጣል።” ብሏል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here