ሐሙስ ሚያዚያ 26 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በፌደራሉ መንግሥት እና እራሱን በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራውና በመንግስት “ኦነግ ሸኔ” ተብሎ በሚጠራው ቡድን መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ በሰሜናዊ ምሥራቅ ዛንዚባር ሙዪኒ የባሕር ዳርቻ ለዘጠኝ ቀናት ያህል በተካሄደው ውይይት፤ ኹለቱን አካላት ካላስማሙ ጉዳዮች መካከል አንዱ የጋራ የሽግግር መንግሥት ምሥረታ መሆኑን ተሳታፊዎች ተናገሩ።
የሰላም ውይይቱ ትናንት ረቡዕ ሚያዝያ 25/2015 ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ኹለቱም ወገኖች በተናጥል ባወጡት መግለጫ ማስታወቃቸው ይታወሳል።
ተደራዳሪዎቹን ካላስማሟቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የጋራ የሽግግር መንግሥት መቋቋም እንደሆነ ሥማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የንግግሩ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
በዚህም በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱትን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስን እና ብልጽግናን ጨምሮ ሌሎች ፓለቲካ ፓርቲዎችን ያካተተ የጋራ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መጠየቁን ቢቢሲ ከተሳታፊዎች ማረጋገጡን ዘግቧል።
የጋራ የሽግግር መንግሥት ምሥረታው በፌደራል መንግሥቱ ተደራዳሪዎች በኩል ተቀባይነት አለማግኘቱንም እነዚህ ምንጮች በዛንዚባር ለሚገኙት የቢቢሲ ጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ተሳታፊዎቹ እንደገለጹት፤ የሽግግር መንግሥት በዋነኝነት የሚቋቋመው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መተማመን እንዲኖር እና አገሪቱ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ እንድትችል የማሻገር ኃላፊነትን እንዲወጣ ለማድረግ መሆኑ ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባወጣው መግለጫ፤ በትናንትናው ዕለት በመጀመሪያው ዙር በነበረው ንግግር በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳልተቻለ ጠቅሶ፤ ውይይቱ በአመዛኙ ገንቢ መሆኑንም አስታውቋል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ውይይቱ መጠናቀቁን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፤ ቁልፍ ብሎ በጠራቸው ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መደረስ አለመቻሉን አመልክቷል።
በዚህ በመጀመሪያው ዙር ውይይት ላይ ከተነሱ ሃሳቦች ሌላኛው በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል ሊደረስ የሚገባው ስምምነት በዘላቂነት ጦርነት በሚያከትም መልኩ፤ እንዲሁም ኹሉንም የሠራዊቱን ፖለቲካዊ እና የጦር ክንፉን ማካተት አለበት ተብሏል።
ኬንያ እና ኖርዌይ በአሸማጋይነት በተሰየሙበት በዚህ የመጀመሪያ ውይይት ላይ ከደቡብ ኦሮሚያ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት መካከል ኹለት ተወካዮች በዚህ ውይይት እንዲሳተፉ መደረጉም ተገልጿል።
በዚህ ውይይት ላይ የተገኙት ስድስት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ተወካዮች ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ልዑካን ሲሆኑ፤ ኹለቱ የሠራዊቱ አባላት በአሸማጋዮቹ በኩል እንዲሳተፉ መደረጉን እና በአጠቃላይም ቡድኑ በስምንት ተወካዮች መወከሉም ተሰምቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥትን በመወከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዴዎን ጤሞቴዎስ ተደራዳሪ ሆነው መቅረባቸውንም ተገልጿል።
በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኩል ደግሞ የታሪክ ምሁሩና በጆርጂያ ስቴት ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን፣ ከኦነግ መስራቾች አንዱና ለበርካታ ዓመታት አመራር የነበሩት ጣሃ አብዲ እንዲሁም የጦሩ አዛዥ ዋና አማካሪ የሆኑት ጂሬኛ ጉደታ ይገኙበታል።
በኦሮሚያ ክልል ለዓመታት የዘለቀውና ለበርካታ ሰዎች ሞት እና መፈናቀል ምክንያት የሆነውን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በፌደራሉ መንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል የመጀመሪያ ዙር ውይይት የተጠናቀቀ ሲሆን ቀጣይ ዙር መቼ ሊካሄድ እንደሚችል አልተገለጸም።
በዚህ የመጀመሪያ ውይይት የተነሱ ጉዳዮች ዝርዝር ባይጠቀሱም፣ ግጭቱን በዘላቂነት እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስቆም እንዲቻል የሰላም ውይይቱን መቀጠል አስፈላጊ ስለመሆኑ መግባባት ላይ መደረሱን ተገልጿል።
በዚህም ኹለቱም አካላት ባወጡት መግለጫ በቀጣይ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያላቸውን ቁርጠኝነት አስታውቀዋል።


