እሁድ ግንቦት 6 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የሰሃላ ሰየምት ወረዳን ከሰቆጣ የሚያገናኘው ብቸኛው የተከዜ የብረት ድልድይ መደርመሱን ተከትሎ፤ የወላድ እናቶች ሕይወት መጥፋት እንደቀጠለ መሆኑን አዲስ ማለዳ ሰምታለች፡፡
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሰሃላ ሰየምት ወረዳ ነዋሪዎች እንደሚሉት፤ በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የሰሃላ ሰየምት ወረዳን ከሰቆጣ ጋር የሚያገናኜው የተከዜ የብረት ድልድይ በመፍረሱ ምክንያት ሪፈር የሚያስፈልጋቸው ነፍሰ ጡር እናቶች ሕይወት እየጠፋ ነው ብለዋል።
ሌላ አማራጭ የሌለው ድልድይ በመፍረሱ እናቶች ወደ ጎንደር እና ባህርዳር ሂደው እንዲታከሙ የሚያስገድዳቸው ቢሆንም፤ የተከዜ ወንዝን መሻገር እንደማይቻል ገልጸዋል። በሕክምና ዕጦት በሦስት ወራት ብቻ የሦስት እናቶች ሕይወት መጥፋቱንም ጨምረው ተናግረዋል።
ድልድዩ በ2013 እንደተደረመሰ አሁንም ድረስ ከአገልግሎት ውጭ ሲሆን፤ እንደ አዲስ ለመስራት የድልድዩን ተሸካሚ መሰረት ለማቆም ቁፋሮ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም ድጋሚ የተከዜ ወንዝ ጠራርጎ እንደወሰደው ነው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።
አዲስ ማለዳ ከዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን መንገድ መምሪያ ኃላፊ ሰለሞን እሸቱ ቆይታ ያደረገች ሲሆን፤ የተከዜ ወንዝ ለበርካታ ዓመታት ሲያገለግል የነበረው የብረት ድልድይ በውሃ መዋጡን በመግለጽ ከ2012 ጀምሮ ማህበረሰቡ ከማንኛውም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ተቋርጦ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የክልሉ መንገድ ቢሮ ለወረዳው ህዝብ ግዜያዊ መጠቀሚያ የሚሆን ተንጠልጣይ ድልድይ እንዲሰርላቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ አለማግኘታቸውን ኃላፊው ተቁመዋል፡፡
ከሦስት ዓመታት በላይ በሰቆቃ ያሳለፈው ህዝብ ለመታደግ ይረዳ ዘንድ ሰው እና እንስሳት ለመሸጋገሪያ የሚጠቅመውን የተንጠልጣይ የብረት ድልድይ በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገባ ካልተደረገ ለከፋ ችግር እንደሚጋለጡ በመጥቀስ በተደጋጋሚ ለአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መንገድ ቢሮ ቢያመለክቱም መፍትሄን እንዳላገኙ ይናገራሉ።
ከአምባጊዮርጊስ-አርባፀጓር እስከ መሸሃ የአስፓልት ዲዛይን 70 በመቶ ደርሶ ለተቋራጭ ጨረታ ወጥቶ ወደ ግንባታ እስኪገባ ድረስ ከመጠበቅ የሰሃለሰየምት ወረዳን ከዞኑ ህዝብ ጋር የሚያገናኘውን መንገድ ወደ ሥራ እንዳይገባ ማድረጋቸው ኹለተኛ በደል እየተፈጸመባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
የአርባፀጓር – መሸሃ – ተከዜ መንገድ ፕሮጀክት ሥራ ከጀመረ ከ13 ዓመት በላይ የተጓተተና በክልሉ ብቸኛው ሳይጠናቀቅ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ መንገድ ከነችግሩ የወረዳውን ህዝብ ከባህርዳር እና ጎንደር በማገናኘት ሲታደግ የነበረ ቢሆንም፤ ድልድዩ መፍትሄ እስኪያገኝ እንኳን ሊሰሩት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የክረምቱ ወቅት ከመግባቱ ጋር ተያይዞ በርካታ የሰው ሕይወት እየጠፋ መሆኑን ገልጸዋል።



