በአማራ ክልል የሐሰተኛ ገንዘብ ዝውውር እየተባባሰ ነው ተባለ

0
587

ቅዳሜ ግንቦት 26 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል በሚገኙ አምስት ዞኖች ሐሰተኛ ገንዘብ በብዛት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንና ይህም በጎንደር፣ ምዕራብ ጎጃም፣ አዊ እና ሰሜን ሸዋ በዋናነት እየተስተዋለ እንደሚገኝ ተገለጸ።

የሐሰተኛ ገንዘብ ህትመቶቹ በብዛት የኹለት መቶ ብር ኖት እና የአሜሪካ ዶላር መሆናቸው ተገልጿል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ብቻ ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ሐሰተኛ የኢትዮጵያ ገንዘብ ኖት እና ከ14 ሺሕ በላይ የአሜሪካ ዶላር በቁጥጥር ሥር መዋሉን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

የሐሰተኛ ገንዘብ ዝውውሩ በቁም እንስሳት ግብይት ላይ ጎልቶ መታየቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ሰዎች ግብይታቸውን ለማሳለጥ ደፋ ቀና ሲሉ ያልጠበቁት ኪሳራ እያጋጠማቸው እንደሆነ ነው የተጠቆመው።

‹‹ተገልጋዮች ግብይታቸውን ጨርሰው ወደ ባንክ ቤት ሲሄዱ ሐሰተኛ ወይም ፎርጅድ ብር እየሆነ እየከሰሩ ናቸው። በድርጊቱ ሲሳተፉ የነበሩ ግለሰቦችንም ከብር ማተሚያ ማሽን ጋር በቁጥጥር ሥር ማዋል የተቻለ ቢሆንም፤ ያልተደረሰባቸው በርካታ ሐሰተኛ ገንዘብ አዘዋዋሪዎች አሉ›› ሲልም የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

በገበያ አዳራሾች እና በቁም እንስሳት ግብይት በርካታ ሐሰተኛ ገንዘብ በየቀኑ እየተያዘ መሆኑን በመጠቆም፤ ዜጎች ግብይታቸውን በጥንቃቄ መከወን እንዳለባቸው ተመላክቷል።

በተያያዘ ዜና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በመዲናዋ በአዲስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ቦታው መርካቶ በረካ ምግብ ቤት አካባቢ ከ79 ሺሕ ብር በላይ ሐሰተኛ ባለ ኹለት መቶ ብር ኖት የያዘን ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ማስታወቁ ይታወሳል። ግለሰቡ ከተያዘበት ቀንና ሰዓት ጀምሮ አስፈላጊውን ምርመራ እየተደረገበት እንደሚገኝ ተጠቅሷል።

ኮሚሽኑ ሐሰተኛ የገንዘብ ዝውውር በማኅበረሰቡ ብሎም በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን በመጥቀስ፤ በእንዲህ ዓይነት ሕገወጥ ተግባር ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦችን ኅብረተሰቡ ጥቆማ በማድረግ አሳልፎ እንዲሰጥ ሲል አሳስቧል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here