የሳምንቱ አንኳር ዜናዎች

0
592

እሁድ ግንቦት 27 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ)

1. በጋምቤላ ከተማ በተሽከርካሪ የሚፈጸም ስርቆትና ዝርፊያ መባባሱ በሕዝቡ ዘንድ ቅሬታ እያስነሳ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰናይ አኩዎር፤ ‹‹በከተማው የንጥቂያና ዝርፊያ ወንጀሎች መባባስ በሕዝቡ ዘንድ ቅሬታ እያስነሳ ነው›› ብለዋል፡፡ አያይዘውም በከተማዋ እየተስፋፋ በመጣው የዝርፊያና መሰል ወንጀሎች በዋናነት ተጠቂዎቹ ሴቶችና አቅመ ደካሞች እንደሆኑ በመግለጽ፤ ወንጀሎችን ለመከላከል ሲባል የፀጥታ ቴክኒክ ኮሚቴው ከግንቦት 20/2015 ጀምሮ ከምሽቱ 3 ሰዓት እስከ ጠዋቱ 12 ሰዓት ባለኹለት እግር ተሽከርካሪ ሞተር ሳይክሎች እንዳይንቀሳቀሱ እገዳ መጣሉን ገልጸዋል።

2. ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ በትግራይ ክልል በአንድ ፓርቲ የተያዘው የፖለቲካ መድረክ እንዲቀየር እየታገልኩኝ ነው አለ፡፡ የፓርቲው የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ  (ነእፓ-ትግራይ) በመጪው ዓመት በክልሉ በሚደረገው ምርጫ ላይ እንደሚሳተፍ ያሳወቀ ሲሆን፤ ‹‹በትግራይ ክልል የተበከለው የፖለቲካ አየር እንዲስተካከል እንፈልጋለን›› ብሏል፡፡ ፓርቲው ግንቦት 21/2015 በሰጠው መግለጫ፤ ‹‹በክልሉ ያለውን አግላይ የፖለቲካ ባህል እንዲቀየር ነው እየታገልኩኝ ያለሁት።›› ሲል ጠቅሶ፣ ‹‹በጤነኛ የፖለቲካ ውድድር ለሕዝባችን አማራጭ ለመሆን በቀጣዩ ምርጫ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆነን እንቀርባለን›› ብሏል፡፡

3. የሐዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከጸጋ በላቸው የጠለፋ ወንጀል ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 6 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ አስታውቋል። የከተማዋ ፖሊስ መምሪያ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እና አጠቃላይ የምርመራ ሂደት ማብራሪያ፤ ‹‹የከተማችን ነዋሪ በሆነችው ጸጋ በላቸው ላይ የደረሰባት የጠለፋ ወንጀል ጉዳዩን አስመልክተው ቤተሰቦቿ በዕለቱ ለመናኸሪያ ፖሊስ በመቅረብ አቤቱታቸውን አሰምተዋል። በዚህም ከጸጋ በላቸው የጠለፋ ወንጀል ጋር የተጠረጠሩ 6 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገ ነው›› ብሏል። ጸጋ በላቸው ግንቦት 15/2015 በሐዋሳ ከተማ ከንቲባ የግል ጠባቂ ኮንስታብል የኋላመብራት ወ/ማሪያም ታግታ ለአስር ቀናት ያለችበት ሳይታወቅ መቋየቷ የሚታወስ ሲሆን፤ ሐሙስ ግንቦት 24/2015 ከአጋቿ ቁጥጥር ነጻ መውጣቷ ይታወቃል። ጸጋ ነጻ ብትወጣም እገታውን የፈጸመው የፖሊስ አባል አለመያዙን የከተማዋ ፖሊስ ገልጿል።

4. ኢትዮጵያን ጨምሮ በ22 የዓለም አገራት አጣዳፊ የምግብ እጥረት ወይም አስከፊ የረሃብ አደጋ እየጨመረ ይሄዳል ተብሏል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት እንዲሁም የዓለም ምግብ ፕሮግራም ባሳለፍነው ሰኞ ባወጡት ሪፖርት፤ ሱዳን፣ ቡርኪናፋሶ ማሊ እና ሃይቲ በአስከፊ የረሃብ አደጋ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸው፤ የደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ናይጄሪያ፣ አፍጋኒስታን እና የመን ጎራ እየተቀላቀሉ ነው ብለዋል፡፡ የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶንግዩ ኩዩ፤ በምግብ እጥረት ሕይወታቸውን የሚያጡ ሚሊዮኖችን ለመታደግ አስቸኳይ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ ከተለመደው አካሄድ ወጣ ብሎ ማሰብ ካልተቻለ የሚፈታ ችግር አይኖርም።›› ሲሉ አመላክተዋል።

5. የራስን ዕድል በራስ የመወሰንን መብት መሠረት በማድረግ በትግራይ ክልል በአስቸኳይ ምርጫ እንዲደረግ የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ጠይቀዋል። ሊቀመንበሩ  የፕሪቶሪያውን ስምምነት መሠረት አድርጎ በክልሉ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ክልሉን መምራት የሚችለው ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት መሆኑን ጠቅሰው፤ ‹‹የተሰጠውን ሥራ አጠናቆ ቀሪ ሥራውን በሕዝቡ ለሚመረጠው አስተዳደር ማስረከብ አለበት።›› ሲሉ በህወሓት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ አስፍረዋል፡፡

6. በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ የሚገኘው የቆቦ ሆስፒታል በጦርነቱ የደረሰበት ጉዳት እስካሁን ምንም ዓይነት እድሳት እንዳልተደረገለት እና በሆስፒታሉ ውስጥ የነበሩ የሕክምና ቁሳቁሶች፣ መድኃኒቶች በሙሉ እንደወደሙ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ በሆስፒታሉ ውስጥ የነበሩ አንቡላንሶች እና የተለያዩ ተሽከርካሪዎች በመዘረፋቸው የሆስፒታሉ ሠራተኞች ከ15 ኪሎ ሜትር በላይ በእግራቸው እየተመላለሱ ናቸው ነው የተባለው። የቆቦ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አሊ ሁሴን፤ በዚህ ወቅት ሆስፒታሉ በሙሉ አቅሙ ወደ ቀድሞው አገልግሎት አለመመለሱን በመግለጽ፤ ይህም በሥራቸው ላይ ከፍተኛ መጉላላት እየፈጠረባቸው መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

7. በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሀዲያ ዞን ምሥራቅ ባደዋቾ ወረዳ፣ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ከሦስት ወራት በላይ ደመወዝ ካለመከፈሉ ጋር ተያይዞ ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ ከ40 በላይ የሚሆኑት መታሰራቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ፡፡ ከመምህራን በስተቀር አብዛኞቹ የመንግሥት ሠራተኞች፤ አሁንም ለተከታታይ ሦስት ወራት ደመወዝ ስላልተከፈላቸው፣ ለከፍተኛ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር መጋለጣቸውም ተጠቅሷል፡፡

8. በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን፣ በጢዮ ወረዳ በጨፌ ሚሶማ ቀበሌ ገበሬ ማኀበር በዴራ አማኑኤል አጥቢያ ቤተክርስቲያን በአሰቃቂ ሁኔታ ግድያ ተፈጽሟል። ግድያው እሁድ ግንቦት 20 ለ21/2015 አጥቢያ ከሌሊቱ 5 ሰዓት ጀምሮ መፈጸሙንም አዲስ ማለዳ ሰምታለች፡፡ ጥቃቱን ያደረሱት ራሳቸውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በማለት የሚጠሩት፤ መንግሥት “ሸኔ” በማለት በአሸባሪነት የፈረጃቸው ታጣቂ ቡድኖች መሆናቸውንም ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በታጣቂ ቡድኑ ግድያ ከተፈጸመባቸው ግለሰቦች መካከል ቄስ ታደለ የቡልጋወርቅ የስድስት ልጆች አባት እና የቤተሰብ ኃላፊ፣ ቄስ ካሱ መንገሻ የአራት ልጆች አባት እና የቤተሰብ ኃላፊ፣ ወጣት እንዳለ የቡልጋወርቅ የአንድ ልጅ አባት፣ አድነው ቶላ የቤተክርስቲያን የጥበቃ ሠራተኛ ሲሆኑ የኹለት ልጆች አባት እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

9. መስከረም ወር 2015 በቁጥጥር ሥር የዋለው ዘመነ ካሴ፤ ግንቦት 25/2015 በባህርዳር ከተማ እና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት “ነፃ ነህ” መባሉን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገልጸዋል። “በከባድ የሰው መግደል ወንጀል” ተከሶ የነበረው የዘመነ ካሴ ጠበቆች የክስ መቃወሚያ ማቅረባቸውን ተከትሎ፤ ዐቃቤ ሕግ መልስ ለመስጠት የክስ ችሎት ለማሰማት ጊዜ ይሰጠኝ ማለቱ ይታወሳል። ፍርድ ቤቱም ዐቃቤ ሕግ በጠየቀው መሠረት ለኅዳር 12/2015 ቀን ዘጠኝ ሰዓት በድጋሜ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ፤ ዘመነ ካሴ ለፍርድ ቤቱ የቃልና የጽሑፍ አቤቱታን እንዲያቀርብ ተደርጓል። በመጨረሻም ግንቦት 25 /2015 ቀን ሰባት ሰዓት በዋለው ችሎት፤ ዘመነ ካሴ ከወንጀል ነፃ ነህ መባሉን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገልጸዋል። አዲስ ማለዳ ይህን ዘገባ እስካጠናቀረችበት ጊዜ ድረስ ዘመነ ከማረሚያ ቤት እንዳልወጣ ማወቅ ተችሏል።

10. ግንቦት 25/2015 መርካቶ በሚገኘው አንዋር መስጊድ አካባቢ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአማኙ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 8 ሰዎች ሲሞቱሠ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁት ደግሞ ከፍተኛ እና መካከለኛ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዘመድኩን ብሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡ ኃላፊው አክለውም ሰልፍ አቀናጅታችኋል የተባሉ ወጣቶችን ከየቤቱ ታድነው እየታሰሩ መሆኑን በመጥቀስ ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here