“መንግሥት ሰብዓዊ መብቶችን የማክበር እና የማስከበር ሃላፊነቱን በአግባቡ ይወጣ” -ኢሰመጉ

0
619

ሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) መንግሥት ሰብዓዊ መብቶችን የማክበር እና የማስከበር ሃላፊነቱን በአግባቡ ይወጣ ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ኢሰመጉ አሳሰበ።

ኢሰመጉ በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጸሙ ነው ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረኤሊያስ ወረዳ፣ በብሄረ ብጹዓን አጼ መልክዓ ስላሴ እና ተክለ ሀይማኖት ገዳማት “በአካባቢዉ የታጠቀ ቡድን እየሰለጠነ ነዉ” በሚል ምክንያት ከጥር 22/2015 ጀምሮ በነበረ የተኩስ ልውውጥ በንጹሃን ላይ ግድያና የአካል ጉዳት መድረሱን ገልጿል።

ወደ ገዳማቱም ከግንቦት 18/2015 ከ4፡00 ሰዓት ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ የከባድ መሳሪያ ተኩስ እየተደረገ መሆኑን የገለጸው ኢሰመጉ፤ በዚህም ምክንያት የአካባቢዉ አርሶ አደሮች በሰላም የግብርና ሥራቸዉን ለመስራት እንደተቸገሩ እና የገዳማቱ መናኝ መነኩሴዎችም ላይ የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸውን አስታውቋል።

እንዲሁም ከገዳሙ ተኩሱን ሸሽተው የሚሄዱ ሰዎችም በአካባቢው በሚገኝ ‹‹ተምቻ›› ተብሎ በሚጠራ ወንዝ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እየሆኑ መሆኑን ከአካባቢው ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለማወቅ መቻሉን የሰብአዊ መብት ድርጀቱ ገልጿል፡፡

በተጨማሪም፤ በጋምቤላ ክልል በኢታንግ ልዩ ወረዳ እና በጋምቤላ ከተማ በቅርቡ ተከስቶ በነበረው የእርስ በርስ ግጭት የሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን የገለጸው ድርጅቱ፤ የአካባቢው እንቅስቃሴ ወደ ቀደሞው እየተመለሰ ቢሆንም፤ አሁንም የጸጥታ ስጋት መኖሩን ከአካባቢው ካሰባሰብኳቸው መረጃዎች ለማወቅ ችያለሁ ብሏል፡፡

በሌላ በኩል፤ መነሻቸውን ከደቡብ ሱዳን በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ጥሰው የሚገቡት የተለያዩ የጎሳ ታጣቂዎች የአርብቶ አደሮችን እንስሳት መዝረፍ፣ ሕጻናትን አፍኖ መውሰድ ከዚህም ሲያልፋ የሰው ሕይወት እስከማጥፋት የሚደርስ ጥቃት እየፈፀሙ እንደሚገኙም ኢሰመጉ በመግለጫው አስታውቋል።

በታጣቂዎቹ የሚያደርሱው ጥቃት ከ2013 ወዲህ በአይነት እና በመጠን እየሰፋ የጉዳቱም መጠንም እየጨመረ እንደሚገኝ በተለያዩ ሪፖርቶቹ የጉዳዩን ትልቅነት እና ስፋት በመጥቀስ ጉዳቱ እንዲቆም ሲያሳስብ መቆየቱን ያስታወሰው ኢሰመጉ፤ በግንቦት 12/2015 በኑዌር ዞን መተሀር አካባቢ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የአካባቢው ነዋሪዋች ሕይወታቸው እንዳለፈ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሰዎችም የከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ሕክምናቸውንም በጋምቤላ ጠቅላላ ሆስፒታል እንደተከታተሉ ማረጋገጡን አስታወቋል፡፡

በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች ማለትም፤ ሀባቦ ጉዱሩ ወረዳ ዳዱ ከተማ፣ ጉዱሩ ወረዳ ኮምቦልቻ ከተማ፣ ጮማን ወረዳ ጎባዬ ከተማ፣ ጅማ ራሬ ወረዳ ዋዩ ከተማ እና አባይጮመን ወረዳ ፊንጫን ከተማ እንዲሁም የፊንጫ ሸለቆ ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ያለበትን አካባቢ ታጣቂ ሃይሎች ግንቦት 06/2015 ጀምሮ እስከ ግንቦት 10/2015 በሀይል ሰብሮ በመግባት ተቆጣጥሮ የነበረ ሲሆን፤ በ13/9/2015 የያዛቸውን አካባቢዎች ለቆ መውጣቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሰመጉ ገልጸዋል፡፡

ታጣቂ ሀይሉ ተቆጣጥሯቸው በነበሩት አካባቢዎች ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውን እና የግልና የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ንብረት መዘረፋቸውን፤ ከነዚህም ውስጥ የተለያዩ የግልና የመንግሥት ባንክ ቤቶች እንደሚገኙበት ኢሰመጉ ከአካባቢው ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለማወቅ መቻሉንም ገልጿል፡፡

በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል የታጠቁ ሃይሎች በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ንፁሃን ሰዎችን በማገት በርካታ ገንዘብ የሚጠይቁ እንዲሁም የሚገሉ ታጣቂዎችን እየበዙ እንደሆነ ከቅርብ ጊዜ የሚቀርቡ አቤቱታዎች ይጠቁማሉም ብሏል፡፡

ከነዚህ አቤቱታዎች ኢሰመጉ እንደተረዳው ታጣቂዎቹ የሚጠይቁት ገንዘብ ከአቅም በላይ እንደሆነ እናም ቤተሰብን ከጭንቀት አልፎ ለመክፈል በሚደረግው ጥረት ከባድ ኢኮኖሚያዊ ችግር ውስጥ እንደከተዉ እና መክፈል ካልቻሉም አንዳንዴ ከፍለውም የታገቱ ቤተሰቦቻቸውን በግፍ አገዳደል እንደሚገድሉባቸውና እሬሳቸውን እንኳን አግኝተው መቅበር እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሰረት መንግሥት በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረኤሊያስ ወረዳ በብሄረ ብጹዓን አጼ መልክዓ ስላሴ እና ተክለ ሀይማኖት ገዳማት እየተፈጠሩ ባለው ተኩስ በንጹሃን ሰዎች ላይ ግድያ፣ የአካል ማጉደል ያደረሱትን በአስቸኳይ ለሕግ እንዲያቀርብ የተየቀው የሰብአዊ መብት ድርጀቱ፤ በአካባቢው ያለ የእምነቱ ተከታይ ሰላሙ ተጠብቆ ማምለክ ይችል ዘንድ መንግሥት ሰብዓዊ መብትን የማክበርም የማስከበርም ሃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስቧል።

በተጨማሪም፤ የጋምቤላ ክልል መንግሥት ግጭቱ በተደጋጋሚ የሚከሰት እና የጎሳ ግጭት በመሆኑ፤ በጎሳዎች መካከል ዘላቂነት ያለው የማህበረሰብ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ችግሮች የሚፈቱበትን መንገድ እንዲያመቻች፤ እንዲሁም፤ ከደቡብ ሱዳን በተለያየ ጊዜ ድንበር አልፎ በመግባት የተለያዩ ጉዳት የሚያደርሱ ጎሳዎችን መንግሥት አስፈላጊውን ትኩረት በመስጠት ድንበሩን እንዲያስከብር እና የአካባቢውን ሰላም እንዲጠብቅ ጠይቋል።

እንዲሁም፤ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በኦሮሚያ አካባቢዎች በተለይም በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ላይ በታጣቂዎች እየፈጸመ ያለውን ግድያ፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ማውደምና ዝርፊያ በአስቸኳይ በማስቆም ማህበረሰቡ በሰላም ወጥቶ የመግባትና በነጻነት የመንቀሳቀስ መብቱን እንዲያስከብር አሳስቧል

እንዲሁም መንግሥት በየቦታው በቡድን በመደራጀት እና በትጥቅ ትግል ውስጥ ሆነው ሰውን በማገት ገንዘብ የሚጠይቁትን ክትትልና ምርመራ በማድረግ ለሕግ እንዲያቀርብና ዜጎች ያለስጋት መንቀሳቀስ እንዲችሉ ያደርግ ዘንድ ኢሰመጉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here