ሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ1444/2015 የሐጅ ጉዞ የመጀመሪያ በረራውን ለሐጅ ተጓዦች የመስገጃና የማረፍያ ቦታን አካትቶ ለዚሁ አገልግሎት ብቻ ታስቦ በተዘጋጀ ተርሚናል በተሳካ ሁኔታ አስጀምሯል፡፡
በማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓቱም ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ሼኽ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ለማ ያደቻ፣ የኦፕሬሽን ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ረታ መላኩ እንዲሁም ሌሎች እንግዶች መገኘታቸውን ከአየር መንገዱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ በዘንድሮው ዓመት ከ15 ሺሕ እስከ 20 ሺሕ ሑጃጆችን ለመላክ ከሳውዲ የእስልምና ጉዳዮች ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን ማስታወቁ ይታወሳል።
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀን ኹለት በረራ የሚያደርግ ሲሆን፤ የሳዉዲ አየር መንገድ ደግሞ በየኹለት ቀኑ አንድ በረራ በማካሄድ የሐጅ ተጓዦችን ለማስተናገድ አየር መንገዶቹ የበረራ መርሀ ግብር ማውጣታቸውን ምክር ቤቱ አስታውቋል።



