አርብ ሰኔ 2 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ጻግብጂ እና አበርገሌ ወረዳዎች ከሚገኙ 27 ቀበሌዎች ውስጥ 19 ቀበሌዎች አሁንም ድረስ ነጻ አለመውጣታቸውን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
ይህን ተከትሎም በጻግብጂ ከሚገኙ 10 ቀበሌዎች ሰባቱ እንዲሁም፤ በአበርገሌ ከ17 ቀበሌዎቹ 12ቱ ነጻ አልወጡም ተብሏል።
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ምህርት መላኩ ቀበሌዎቹ በማን ቁጥጥር ሥር ናቸው ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “በቀበሌዎቹ የመንግሥት መዋቅር የለም ማለት ሌላ አካል አለ ማለት ነው፤ ሄጄ ባላረጋግጥም ነጻ አልወጣም ማለት በሌላ ሃይል ተይዟል ማለት ነው።” ሲሉ ተናግረዋል።
እንዲሁም ነጻ ከወጡት ኹለቱ ቀበሌዎች ተፈናቅለው ለነበሩት 67 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች አንድ ዙር የምግብ እህል ስርጭት መደረጉን ገልጸው፤ በአሁኑ ሰዓት ኹሉም ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው ተመልሰዋል ብለዋል።
በቀበሌዎቹ የሚገኙ የወረዳው ጤና ጣቢያ እና ባንኮች የተወሰነ ጥገና ተደርጎላቸው ወደ ሥራ መግባታቸውን የገለጹት ሃላፊው፤ ወደ ገጠራማ ሥፍራዎች በመሰረት ልማቶች ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ስለሆነ በቀላሉ ተጠግነው አገልግሎት መስጠት አለመቻላቸውን አመላክተዋል።
በተጨማሪም በወቅቱ በነበረው ጦርነት ምክንያት ማኅበረሰቡ ምርት ማምረት እንዳልቻሉ እንዲሁም ምንም አይነት ድጋፍና እርዳታ እንዳልተደረገላቸው ገልጸው፤ “እርዳታ እንዲደረግላቸው ከበላይ አካል ብንጠይቅም ምላሽ አላገኘንም።” ብለዋል።
በአካባቢው የህወሓት ሃይሎች እና የአገው ታጣቂዎች እንደሚንቀሳቅሱ ይነግራል።
መነሻውን በትግራይ ክልል አድርጎ ለኹለት ዓመታት የዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት በአማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች ተስፋፍቶ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውደመት ማስከተሉ ይታወቃል።



