ማክሰኞ ሰኔ 6 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) አንድ የእስራኤል ባለስልጣን “ቤተሰቦቻችሁን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ለማምጣት አግዛችኋለሁ” በማለት ከስድስት ሴቶች ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጽሟል የሚል ክስ እንደተመሰረተበት ተገልጿል። ባለስልጣኑ በሦስቱ ክሶች ብቻ ጥፋተኛ መባሉ ተነግሯል።
የእስራኤል የሕዝብ እና ኢሚግሬሽን ተቋም ውስጥ ባለስልጣን መሆኑ የተገለጸው ሊዮር ሰሎሞን የተባለ ግለሰብ፤ በኢኮኖሚ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከነበሩት እና በአገሪቷ ቤተሰብ አልባ እንደሆኑ ከተናገሩት ከእነዚህ ሴቶች ጋር በማታልል ግንኙነቱ ሊመስርት እንደቻል ተጠቁሟል።
በሴቶች ላይ ባደረሰው ጾታዊ ጥቃት ከቀረበበት ክስ በተጨማሪም፤ ወደ ኢሚግሬሽን ባለስልጣን የመረጃ ቋት በመግባት ለጓደኛው የግለሰብን የግል መረጃ እንዲያኝ ረድቷል በሚል መከሰሱንም ነው እየሩሳሌም ፖስተ የዘገበው።
ዐቃቤ ሕግ ግለሰቡ ስልጣኑን ተጠቅሞ በሴቶች ላይ ያደረሰውን ችግር በመግለጽ፤ በኹለት ዓመት እስራት እንዲቀጣ ጠይቋል።
እንዲሁም ከሦስት ሴቶች የወሲብ ጉቦ በመቀበል እና በድርጅቱ የመረጃ ቋት ውስጥ ያለውን የግል መረጃ በመጣስ በሚል በቀረበበት ክስ እሁድ ዕለት ለዘጠኝ ወራት የማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጥ ተፈርዶበታል ተብሏል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በእስራኤል በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች የሚኖሩ ሲሆን፤ የተለያዩ አድሎዓዊ እና ዘር ተኮር ጥቃት እንደሚፈጸምባቸውም ይጠቀሳል።



