“ልጅቷን ቢሠጡኝ ባለኝ አቅም ከልጆቸ ጋር አብሬ ማሳደግ እፈልጋለሁ” ዋና ሳጅን ሙሉጎጃም ሽቤ

0
592

ማክሰኞ ሰኔ 6 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ዋና ሳጅን ሙሉጎጃም ሽቤ በባህርዳር ከተማ 6ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ የትራፊክ ፖሊስ ሲሆኑ፤ ሰኔ 5/2015 በሥራ ቦታዋ ተጥላ የተገኘች የ5 ቀን እድሜ ያላት ሕጻን በርሃብ ስታለቅስ የእናትነት አንጀታቸው አልችል ስላላቸው ጡት በማጥባት የሕጻኗን ርሃብ አስታግሰው ከሞት ታድገዋል፡፡

የ6ኛ ፖሊስ ጣቢያ የሕጻኗን ጤንነት በሕክምና ካረጋገጠ በሗላ ለሕጻናት ማሳደጊያ ድርጅት አስረክቧል፡፡

ዋና ሳጅን ሙሉጎጃም የሦስት ልጆች እናት ሲሆኑ፤ የአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር ጡት የሚያጠቧት ሕጻን ልጅ ስላላቸው ጡቱን ለማጥባት ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው ገልጸዋል፡፡

ሕጻኗን ጡት አጥብተው ሕይወቷን ማትረፍ በመቻላቸው መደሰታቸውን በመግለጽ፤ ሕጻኗን ባላቸው ደመወዝ ከወለዷቸዉ ልጆች ጋር በጋራ ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸውና ሕጻኗ እንድትሰጣቸው መጠየቃቸውን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሸን አስታውቋል፡፡

የ6ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ ሀላፊ ኮማንደር ሀብታሙ አሰፋ በበኩላቸዉ፤ ዋና ሳጅን ሙሉጎጃም ያጠቧትን ሕጻን እንዲያሳድጓት ለመስጠት ከሴቶችና ሕጻናት መምሪያ ጋር በመነጋገር ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ረዳት ሳጅን ቤተልሔም ምትኩ የተባሉ በድሬዳዋ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ውስጥ ፖሊስ መሬት በሚባለው ፖሊስ ጣቢያ መርማሪ፤ ከተወለደ አንድ ወር የሆነውን እና በድሬዳዋ ከተማ 09 ቀበሌ ገራዳ በሚባል አካባቢ ባለ ድልድይ ሥር ተጥሎ የተገኘውን ልጅ ጡታቸውን በማጥባት “ሕይወቱን መታደጋቸውን” የፖሊስ መምሪያው ማስታወቁ ይታወሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here