ማክሰኞ ሰኔ 6 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ከሶማሊያ ግጭት በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ስደተኞች ውስጥ 70 በመቶ ገደማ የሚሆኑት መጠለያ ባለማግኘታቸው ሜዳ ላይ እንደሚያድሩ ተገልጿል።
ይህ የሆነው በገንዘብ እጥረት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ለስደተኞች ያስፈልጋል ከተባለው 116 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ የተገኘው ኹለት በመቶ ብቻ መሆኑ ተጠቅሷል።
ይህን ተከትሎም ለስደተኞች ከሚያስፈልገው መጠለያ 30 በመቶ ብቻ በመሟላቱ ሌሎቹ በአንድ ቦታ ተጨናንቀው በዛፎች ሥርና ሜዳ ላይ እንደሚኖሩ ተመላክቷል።
ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ከ100 ሺሕ በላይ ስደተኞች መካከል፤ 20 ሺሕ ያህሉ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን ቦኦ ወረዳ ሚርቃን ቀበሌ በሚገኝ መጠለያ ጣቢያ እንዲገቡ መደረጋቸው ነው የተገለጸው።
ለእነዚህ ስደተኞች የመጠለያ፣ ምግብና ሕክምና አገልግሎት ባለማግኘታቸው ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ፤ በኢትዮጵያ መንግሥት፣ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ እንዲሁም በሰብዓዊ እርዳታ ሰጭ አጋሮች ድጋፍ ወደ ሚርቃን ቀበሌ እንዲዛወሩ መደረጋቸው ተመላክቷል፡፡
ሆኖም በሶማሌ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በዛፍ ሥር እና ሜዳ ላይ የሚያድሩ 70 በመቶ ገደማ የሚሆኑ የሶማሊያ ስደተኞች ለዘረፋ እንዲሁም ለፆታዊ ጥቃቶች መጋለጣቸው ተገልጿል።
በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ አንድ ሚሊዮን ገደማ ስደተኞች መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ለስደተኞች የሚቀርበው ድጋፍ ግን በጣም አነስተኛ ነው ሲል ዴቭዲስኮርስ በድህረገጹ አስነብቧል።
ከምግብ፣ መጠለያና ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶች አቅርቦት በተጨማሪ፣ በተለይ እንክብካቤ ለሚፈልጉ ጸኑ ሕመምተኞች፣ ነፍሰ ጡር እናቶች እንዲሁም ከአስገድዶ መደፈር ለተረፉ እና ሌሎች ፆታዊ ጥቃቶች ለተፈጸሙባቸው ሴቶች አገልግሎት ለማቅረብ አስቸጋሪ መሆኑ ተመላክቷል።
ስለሆነም ስደተኞቹ የሞት አፋፍ ላይ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግላቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኤጄንሲ እንዲሁም ሌሎች የሰብዓዊ ድጋፍ አጋሮች አሳስበዋል።
ከባለፈው የካቲት ወር ጀምሮ በርካታ ሕዝብ ከሚኖርባት ሶማሌላንድ ላሶን ተብሎ በሚጠራ ቦታ እየተካሄደ ያለውን ግጭት እና ሁከት በመሸሽ፤ በ100 ሺሕዎች የሚገመቱ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ተገልጿል፡



