200 ወጣቶች ወደ አውሮፓ ትሄዳላችሁ ተብለው ከፍተኛ ገንዘብ መጭበርበራቸውን ገለጹ

0
819

ማክሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) 200 የሚጠጉ ወጣቶች “ኤክስክሉሲቭ ትራቭል” በተባለ ኤጀንሲ በኩል ወደ ተለያዩ የአውሮፓ አገራት ትሄዳለችሁ ተብለው 20 ሚሊዮን ብር መጭበርበራቸውን ገለጹ፡፡

ተጭበርብረናል ያሉ ወጣቶች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፤ መቀመጫውን አዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ደንበል ያደረገው “ኤክስሉሲቭ ትራቭል” ወደ አወሮፓ እና ወደ ተለያዩ አገራት አልካችኋለሁ በማለት ገንዘብ ከሰበሰበ በኋላ አድራሻውን አጥፍቶ እንደጠፋባቸው ተናግረዋል፡፡

ወጣቶቹ የጉዞ ሂደቱ እንዳለቀና ኤምባሲ ሄደው ቃለ መጠይቅ እንዳደርጉ ከ“ኤክስሉሲቭ ትራቭል” በተሰጣቸው ቀጠሮ መሰረት ወደ ኤምባሲ ሲሄዱ “ድርጅቱን አናውቀውም” እንደተባሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡ ይባስ ብሎ ወጣቶቹ የሄዱባቸው ኤምባሲዎች “የምናውቀው ነገር የለም” ካሏቸው በኋላ ብር የከፈሉትን አካል ሲጡቁ፣ “ስህተት ተፈጥሮ ነው ይስተካከላል” በማለት ፓስፖርታቸውንና የ“ኮቴ” ብሎ ከየአንዳንዳቸው ስምንት ሺሕ ብር ከተቀበለ በኋላ ስልኩን አጥፍቶ ጠፍቷል፡፡

“ኤክስሉሲቭ ትራቭል” በሚል ስያሜ ሕጋዊ ኤጀንሲ እንደሆነ ወጣቶቹን በማሳመን ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ሰብስቦ የጠፋው አካል አድራሻውን ያጠፋው ከሰኔ 6/2015 ጀምሮ ሲሆን፤ ከጠፋ በኋላ ሕጋዊነቱ ሲጣራ የንግድ ፈቃዱና ያስመዘገበው የቤት ቁጥሩ ሐሰተኛ እንደሆነ ታውቋል፡፡

አዲስ ማለዳ ወጣቶቹ “ተጭበርብረንበታል” ያሉትን ሀሰተኛ የንግድ ፈቃድ የተመለከተች ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ አላውቀውም ያለው የንግድ ፈቃድ ላይ በባለቤትነት የተጠቀሰው የግለሰብ ሥም ሲሳይ አበበ ማስረሻ የሚል ነው፡፡

ወጣቶቹ በሥም ለተጠቀሰውና ራሱን ሕጋዊ ኤጀንሲ አደርጎ ለቀረበው አካል፤ በተለያዩ ጊዜያት ከመመዝገቢያ እስከ ሂደት ማስጨረሻ ለስምንት ወር ገዘንብ ሲከፍሉ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ከሦስት ወር እስከ አራት ወር ያልቃል የተባለው ወደ አውሮፓ አገራት የመሻገር ጉዞ፤ ስምንት ወር ከፈጀና “የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሳችኋል” ከተባሉ በኋላ ገንዘቡን የሰበሰበው አካል አድራሻውን አጥፍቶ ጠፍቷል፡፡

ራሱን ሕጋዊ አስመስሎ ሲንቀሳቀስ የነበረው አካል፤ ወጣቶቹ አሳማኝ ነው ያሉትን ስልት በመጠቀም ከየአንዳንዳቸው ከ100 ሺሕ እስከ 400 ሺሕ ብር መሰብሰቡ ታውቋል፡፡ ክፍያው ወጣቶቹ ይሄዱበታል እንደተባለው አገር የሚለያይ ሲሆን፤ አብኛዎቹ ወጣቶች ሙሉ ክፍያ ፈጽመዋል ተብሏል፡፡

አዲስ ማለዳ ያነጋገረችው የዚህ ድርጊት ሰላባ የሆነ ወጣት አጠቃላይ ከፍያ 218 ሺሕ ብር መሆኑን ተናግሯል፡፡ በዚህ መሰረት ለሂደቱ ማስጀምሪያ 25 ሺሕ ብር፣ የሥራ ፈቃድ ማረጋጫ 104 ሺሕ ብር የከፈለ ሲሆን፣ ለከፈለው ብር ዋስትና ተብሎ ቼክ ተቀብሎ እንደነበር ይገልጻል፡፡

አብዛኛዎቹ ወጣቶች የቀረበላቸውን ማስረጃ በማመን ሙሉ ክፍያ እንደፈጸሙ የሚገልጸው ይህ ወጣት፤ እሱን ጨምሮ ወጣቶቹ ለከፈሉት ገንዘብ ማስተማማኛ ተብሎ ቼክ የተሰጣቸው ቢሆንም፣ ቼክ የተፈረመበት አካውንት ባዶ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

አዲስ ማለዳ “ኤክስሉሲቭ ትራቭል” ስለተባለው አካል ባደረገችው ማጣራት፤ “በሥራ ወደ ተለያዩ አገራት እንልካለን” በሚል በተለይ የዩኒቨርስቲ ምሩቅ ወጣቶችን በስፋት ሲመዘግብ እንደነበር ተረድታለች፡፡

በንግድ ፈቃዱ ላይ ሥሙ የተጠቀሰው ግለሰብ ስልኩን አጥፍቶ ከጠፋ በኋላ ከሰራተኞቹ ጋር በዋትስአፕ መልዕክት ሲለዋወጥ የነበረ ሲሆን፤ ካለፈው አርብ ጀምሮ ግንኙነቱን አቋርጦ መጥፋቱን በሥሩ ሲሰሩ የነበሩ ሰዎች ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here