በአምስት የምስራቅ አፍሪካ አገራት ከ30 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተባለ

0
346

ማክሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት በአምስት የምስራቅ አፍሪካ አገራት ከ30 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) አስታውቋል።

የድርጅቱ የአየር ንብረት ትንበያ እና ትግበራ ማዕከል ባወጣው ሪፖርት፤ በዘንድሮው የፈረንጆች ዓመት በዩጋንዳ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያና ሱማሊያ ከ30 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ብሏል።

ከ2020 ጀምሮ የድጋፍ ፈላጊዎች ቁጥር በየዓመቱ በ10 ሚሊዮን ሰዎች እየጨመረ መምጣቱም ተመላክቷል።

በፈረንጆች 2022 ከኤርትራ ውጭ ባሉ ሰባት የኢጋድ አባል አገራት በ2021 የነበረው የተረጂዎች ቁጥር በ13 ሚሊዮን ጨምሮ፤ ከ55 ሚሊዮን በላይ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ፈላጊ ሰዎች እንደነበሩ ተጠቁሟል።

የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ትንበያ እና ትግበራ ማዕከል፣ የዓለም አቀፍ የምግብ ቀውስ ሪፖርት፤ በኢጋድ ቀጠና ትኩረት አድርጎ ለዘንድሮው የፈረንጆች ዓመት ያጠናቀረውን መረጃ ይፋ ባደረገበት ወቅት፣ በኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና ሱዳን ያጋጠመው አስከፊ የምግብ እጥረት ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ተከስቶ የማያውቅ ነው ብሏል።

በኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሱማሊያና ዩጋንዳ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ምክንያት ከ35 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በከፍተኛ የምግብ ቀውስ ውስጥ መሆናቸውም ተመላክቷል።

እንዲሁም በምጣኔ ሀብት ውድቀት የተነሳ በጅቡቲ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን 19 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች በአስከፊ የምግብ እጥረት ውስጥ መሆናቸው ነው የተገለጸው።

በሶማሊያ በድርቅ፣ ግጭትና በዋጋ ግሽበት የተነሳ በፈረንጆች 2022 የነበረው 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን የተረጂዎች ቁጥር በዓመቱ በ18 በመቶ ማሻቀቡ ተጠቅሷል።

5 ነጥብ 4 ሚሊዮን የኬንያ ዜጎችም በዋናነት በድርቅና በዋጋ መናር ምክንያት በከፋ የምግብ ቀውስ ውስጥ ናቸው ተብሏል።

ስለሆነም በኢጋድ ቀጠና ያለውን የምግብ ቀውስ ለመፍታት ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ መንግስታት፣ ሲቪል ድርጅቶችና የሚመለከታቸው አካላት አስቸኳይና የተቀናጀ ትብብር ማድረግ እንዳለባቸው ተጠቁሟል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here