የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ሠራተኞች ሥራ ማቆማቸው ተገለጸ

0
499

በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኘው የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል የጤና ባለሙያዎች የትርፍ ሰዓት ክፍያ እየተከፈለን አይደለም በማለት ከዛሬ ሐምሌ 04/2015 ጀምሮ ሥራ ማቆማቸውን ለአዲሰ ማለዳ ገልጸዋል።

በሆስፒታሉ ለሚሰሩ 500 ሠራተኞች ከሚያዚያ 2015 ጀምሮ የትርፍ ሰዓት ደመወዝ እየተከፈለ ባለመሆኑ፣ በተደጋጋሚ ቅሬታችንን ብናቀረብም የሚሰማን አካል ስለሌለ ሥራ ለማቆም ተገደናል ነው ያሉት።

ታካሚ በየሰዓቱ ስለሚመጣ ግዴታ የትርፍ ሰዓት መሰራት አለበት ያሉት ሠራተኞች፣ ነገር ግን የትርፍ ሰአት ክፍያችን እየተከፈለን ባለመሆኑ ሥራ አቁመናል ሲሉ አክለዋል፡፡

የትርፍ ሰዓት ክፍያው እነዲከፈለን በተደጋጋሚ ለሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ብንናገርም ‹‹ጉዳዩ ከአቅሜ በላይ ነው፡፡ የበጀት እጥረት አለብን ›› የሚል ምላሽ ነው የተሰጠን ብለዋል።

የሆስፒታሉ ሠራተኞች ሥራቸውን ከማቆማቸው ጋር ተያይዞ በሆሰፒታሉ አስቸኳይ የህክምና እርዳታ የሚፈለጉ ሰዎች፤ ወላድ እናቶች፤ ሕጻናት እንዲሁም ሌሎች የህክምና አገልግሎት የሚፈልጉ ሁሉ  እየተጉላሉ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የሚመለከተው አካል ምላሽ ሰጥቶ፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያው በአግባቡ እስካለተከፈላቸው  ሠራተኞች ወደ ሥራ እንደማይመለሱም ነው የተናገሩት።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለማግኘት ወደ ጅንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ማቲዎስ ጋርሾ ብትደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ማእከል ሠራተኞች እንዲሁም በአማራ ክልል አዊ ዞን ባንጃ ወረዳ የሚገኙ ስድስት ጤና ጣቢያዎች የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች የትርፍ ሰዓት ክፍያ እየተከፈላቸው ባለመሆኑ፣ ሠራተኞች ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩ እንቅፋት እንደሆነባቸው ያቀረቡትን ቅሬታ አዲስ ማለዳ መዘገቧ የሚታወስ ነው፡፡

በቅርቡ በተለይም 11ኛ ክልል ሆኖ በተቋቋመው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል፣ በሌሎች የሥራ መስኮች በሚሰሩ የመንግሥት ሠራተኞች ዘንድም ተደጋጋሚ የደመወዝ አልተከፈለንም ቅሬታዎች በስፋት ሲቀርቡ ይስተዋላል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here