የኦሮሞ ሕዝብ በደሙ እና በአጥንቱ ያመጣውን ለውጥ ለማንም አሳልፎ አይሰጥም ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ፡፡ ፕሬዝደንቱ ይህን ያሉት የክልሉን የ2015 የመንግሥት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለጨፌ ኦሮሚያ በትናትናው ዕለት ባቀረቡበት ወቅት ነው፡፡
ከጨፌው አባላት “የኦሮሞ ሕዝብ ባለ ጊዜ ተረኛ እየተባለ በሌሎች አካላት ተርጋ ተጥፎበታል፣ ሕዝቡስ ከሌላው የኢትዮጵያ ዜጋ ምን የተለየ ጥቅም አግኝቷል እርሶስ ይህን እንዴት ይመለከቱታል” ተብለው ተጠይቀዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱም ለተጠየቁት ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የኦሮሞ ሕዝብ ደም እና አጥንቱን ገብሮ ለውጥ ማምጣቱን በመጠቆም ያመጣውን ለውጥ ለማንም አሳልፎ አይሰጥም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ክልሉ ለብዙ ዓመታት በመልካም አስተዳደር ችግር በብልሹ አሰራር በሙስና ሕዝቡም መሪ አጥቶ በገዛ ንብረቱ ላይ የባለቤትነት መብቱን ተነፍጎ ማንም እንደፈለገ ሲያደርገው ኖሯል ብለዋል፡፡ ከለውጡ በኋላ ጥቂትም ብትሆን የሕዝቡን ጥያቄ መመለስ ስንጀምር እና ከዕለት ዕለት ዕድገት እያስመዘገብን ስንመጣ ጠላቶቻችን “ባለ ጊዜ፣ ባለተራ” በሚሉ ቃላት አንገታችንን ሊያስደፉን ይሞክራሉ ሲሉ አብራርተዋል፡፡
“እኛም ለጠላቶቻችን መንገር የምንፈለገው አትድከሙ ከዚህ በኋላ በእደዚህ አይነት የመንደር ወሬ አንገታችንን የምንደፋ እና የጀመርነውን የብልጽግና ጉዞ የምናቋራጥ አደለንም ልንላቸው እንፈልጋለን” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከኦሮሞ ማኅበረሰብ ስለወጡ ብቻ በጭፍን ጥላቻ መንገዳቸው ላይ በመቆም የክፋት እጃቸውን የሚዘረጉ አካላትን በትዕግስት ሆነን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ እንነግራቸዋለን፣ አምቢ ብለው በጀመሩት የተንኮል ጎዳና የሚቀጥሉ ከሆነ ግን የዘረጉትን የክፋት እጃቸውን እንቆርጣለን” ሲሉም ሽመልስ አስጠንቅቀዋል፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ በተለየ ያገኘው ጥቅም የለም ያሉት ሽመልሽ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የአገሪቱ ዜጎች በክልሉ እንደሚኖሩ አስታውስው፣ የኦሮሞ ሕዝብ የሚያገኘውን ማንኛውንም አገልግሎት ያገኛሉ ብለዋል፡፡ በክልሉ ያላችሁ አመራሮችም እየተደረገ ያለው የስም ማጥፋ ዘመቻ ሳያስደነግጣችሁ በምትሰሩት መልካም ስራም ብዙ ሳትኩራሩ ይህን ሕዝብ እንድናሻግር ጥሪዬን አስተላልፋለሁ ብለዋል፡፡



