ኢትዮጵያ ብሪክስን ብትቀላቀል ከምዕራባውያን የምታገኘው እርዳታ እና ኢንቨስትመንት ሊቀንስ እንደሚችል ተጠቆመ

0
488

ኢትዮጵያ የብራዚል፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ህንድ እና ደቡብ አፍሪካ ህብረት የሆነውን ብሪክስ ብትቀላቀል ከምዕራቡ ዓለም የምታገኘውን እርዳታ እና ኢንቨስትመንት ሊቀንስ እንደሚችል ተጠቁሟል።

ሆኖም የኢትዮጵያን መልካምድራዊ ጠቀሜታ ከፍ በማድረግ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት የተሻለ ሊያደርገው እንደሚችል ተመላክቷል። 

በትሪንቲ ኮሌጅ የጂኦግራፊ ፕሮፌሰር ፓድራይግ ካርሞዲ በዚህ ጉዳይ ላይ ባደረጉት ጥናት፤ ኢትዮጵያ የብሪክስን አገራት በንግድ፣ በፖለቲካ እና በባህል ትብብርን የሚያበረታታ ነፃ ዓለም አቀፍ ድርጅት መቀላቀሏ የተለያዩ አዎንታዊ እና አሉታዊ አንድምታዎች እንደሚኖሩት ለ”ዘ ኮንቭርሴሽን” ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከአምስት በመቶ በላይ ዓመታዊ የምጣኔ ሀብት እድገት በማስመዝገብ በአፍሪካ ፈጣን ዕድገት እያሳዩ ካሉ አገራት ተርታ የምትመደብ በመሆኑ፤ ብሪክስን መቀላቀል የተሻለ ትብብርን የሚያስገኝ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ ጋር በገንዘብ ድጋፍ ላይ እየተደራደረ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ብሪክስን ብትቀላቀል የመደራደር አቅሙን ከፍ ሊያደርግ ይችላል ሲሉ ጠቁመዋል።

በዚህም አይኤምኤፍን የሚቆጣጠሩት ምዕራባውያን አገራት ኢትዮጵያን ከብሪክስ ማራቅ የበለጠ ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት ማጥበቅ እንዳይሆን ሲሉ ጥንቃቄ ያደርጋሉም ብለዋል።

በአገራት ላይ ጣልቃ አለመግባት ከብሪክስ መሰረታዊ መርሆዎች አንዱ በመሆኑም፤ ኢትዮጵያ ማህበሩን ብትቀላቀል የውጭ ጣልቃ ገብነት ከማስቀረት አንጻር ጥቅም ይኖረዋል ተብሏል። 

እንዲሁም በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ “ጦርነት አራማጅ ናቸው” በሚል የደረሰባቸውን ከባድ ትችት፤ ብሪክስን በመቀላቀል መንግሥታቸው አሁንም በአንዳንድ አስፈላጊ የዓለም ኃይሎች ፖለቲካዊ ተቀባይነት እንዳለው ለማሳየት ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሪክስን መጨረሻ ላይ ከተቀላቀለችው ከደቡብ አፍሪካ በግማሽ ያነሰ ምጣኔ ሀብት ቢኖራትም፤ ነገር ግን የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ መሆኗ እንዲሁም አዲስ አበባ የአፍሪካ ዋና ዲፕሎማሲያዊ መዲና መሆኗ በአንጻራዊነት በተሻለ እድል ህብረቱን ለመቀላቀል እንደሚያግዛት ተጠቁሟል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ ብሪክስን ለመቀላቀል ይፋዊ ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን፥ ህብረቱ ባቀረበችው ጥያቄ ላይ ከመጭው ክረምት በኋላ ውሳኔውን ሊያሳውቅ እንደሚችል ተመላክቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here