ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በግብጽ ተገናኝተው መምከራቸው ተነገረ

0
839

አርብ ሐምሌ 7 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በግብጽ ዋና ከተማ ካይሮ ላይ የተገናኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የኤርትራው ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ በወታደራዊ ኃይሎች ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ስለገባችው ሱዳን መነጋገራቸው ተሰምቷል፡፡

የኤርትራ መረጃ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል የመሪዎቹን መገናኘት አስመልቶ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ረቡዕ ምሽት ላይ የተገናኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና ፕሬዘዳንት ኢሳያስ በሱዳን ቀውስ ላይ ትኩረት ያረገ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ፤ ኹለቱ መሪዎች የኢትዮጵያና የኤርትራን ቀጣይ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ገልጸዋል።

መሪዎቹ በየፊናቸው ከግብጽ ፕሬዝደንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውም የተሰማ ሲሆን፤ በዋናነት ካይሮ ላይ ካሰባሰባቸው ከሱዳን ቀውስ በተጨማሪ በሌሎች ቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መምክራቸው ታውቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ረቡዕ ዕለት ከአልሲሲ ጋር ተገናኝተው፤ በኹለቱ አገራት የኹለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ እና ኤርትራን ጨምሮ የሱዳን ጎረቤት አገራት መሪዎች በሱዳን ወቅታዊ ኹኔታ ላይ ለመምከር ወደ ካይሮ መቅናታቸው ይታወቃል።

መሪዎቹ በትናንቱ ውሏቸው የሱዳን ቀውስ ላይ ትኩረት አድረገው ሲመክሩ የዋሉ ሲሆን፤ ጦርነቱ የሱዳንን ሕዝብ ለመከራ ከመጋበዙ በተጨማሪ ለጎረቤት አገራት የተረፈ ቀውስ መፍጠሩን አንስተዋል፡፡

በጀነራል መሐመድ ሃምዳን ዳግሎ በሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እና በጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን በሚመራው የሱዳን ብሔራዊ ጦር መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት፤ ከሦስት ሺሕ በላይ ዜጎችን ሕይወት ቀጥፏል፡፡

አሁንም በቀጠለው ጦርነት ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሱዳንያዊያን ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውንና ከ700 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ወደ ጎረቤት አገራት ተሰደው መጠለያ በመፈለግ ላይ መሆናቸውን የመንግሥታተቱ ድርጅት መረጃ ያመላክታል፡፡

ኹለቱ ተፋላሚ ኃይሎች፣ በአስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲያውጁና ወደ ውይይት እንዲመለሱ የተለያዩ አካላት ቢማጸኗቸውም እስካሁን ጦርነቱን አቁመው ለንግግር መቀመጥ አልቻሉም፡፡

ለረዥም ጊዜ ሰላምና መረጋጋት ርቋት የኖረችው ሱዳን፤ አሁን ላይ የገጠማት ግጭት ወደለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት እንዳያመራ ተሰግቷል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here