የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር እና ዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤትን ጨምሮ በስምንት ከፍተኛ የመንግሥት ተቋማት ላይ ክስ መመስረታቸውን ገልጸዋል።
ፓርቲዎቹ ክሱን የመሰረቱት የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል መንግሥት፣ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት እንዲሁም የወላይታ ዞን አስተዳደር፣ የወላይታ ዞን ምክር ቤት እና የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ላይ መሆኑን ትናንት ሐምሌ 07/2015 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
የተመሰረተው ክስ የዎላይታ ሕዝብ ከታህሳስ 08/2011 ጀምሮ ራሱን የማስተዳደር መብቱን በመጠቀም በክልል ለመደራጀት ያቀረበውን ጥያቄ ያለመመለስን ጨምሮ፤ እስካሁን ለተፈጸሙና እየተፈጸሙ ላሉ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተገቢውን ፍትሕ የሚጠይቅ መሆኑን የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር አማኑኤል ሞጊሶ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ሊቀመንበሩ አክለውም፣ የዎላይታ ብሔር ክልላዊ መንግሥት እስከ 1987 ድረስ ክልል ዘጠኝ በመባል ተደራጅቶ እንደነበር ገልጸው፣ “የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል መዋቅር ሲደራጅ፣ ወላይታ በዞን አስተዳደር እንኳን እንዳይደራጅ መብት ተነፍጎት ስለነበር ሕዝቡ በየጊዜው ባደረገው መራር ትግል በ1993 ወላይታ ዞን በመባል ተደራጅቶ ቆይቷል።” ሲሉ አስታውሰዋል።
ሆኖም በተለይ ነሐሴ 2012 የዎላይታ ሕዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር በሰላማዊ መንገድ ጥያቄ ቢያቀርብም፣ የጸጥታ አካላት በወሰዱት ሕግን ያልተከተለ እርምጃ ከ38 በላይ ሰዎች መገደላቸዉንና ከ200 በላይ ሰዎች ቀላልና ከባድ አካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የብሔሩ አባላት ለሕገ ወጥ እስርና ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መጋለጣቸውን አንስተው፤ በዚህና የማህበረሱቡ የራስን በራስ የመወሰን ሕገመንግሥታዊ መብት አለመከበር የተነሳ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የመሰረታዊ መብቶችና ነጻነት ችሎት ክስ መቅረቡ አመላክተዋል።
በዚህም ፍርድ ቤቱ ትናንት ሐምሌ 07/2015 በዋለው ችሎት፤ ከተከሳሾቹ መካከል ብልፅግና ፓርቲ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሳይቀርቡ መቅረታቸውን እንዲሁም ከቀረቡት ስድስት ተቋማት መካከል በፅሑፍ መልስ ያቀረበው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ መሆኑ ተነግሯል፡፡
አምስቱ ተከሳሽ “በቂ ጊዜ አልነበረንም” በሚል ተለዋጭ ቀጠሮ መጠየቃቸውን ተከትሎም ፍርድ ቤቱ ለሐምሌ 28/2015 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ነው የተገለጸው።
መንግሥት ባቀረበው የክላስተር አደረጃጀት መሰረት፣ ወላይታ ዞንን ጨምሮ ስድስት ዞኖችንና አምስት ልዩ ወረዳዎችን ያካተተ <<ደቡብ ኢትዮጽያ>> በሚል ስያሜ 12ኛ ክልል መመስረቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከቀናት በፊት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።



