ኤችአይቪ ኤድስን ማስወገድ እንደሚቻል ተጠቆመ

0
681

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስከ ቀጣዩ የፈረንጆች 2030 የኤችአይቪ ኤድስ ወረርሽኝ በዓለም ላይ እንዲያበቃ ማድረግ ይቻላል ሲል አስታውቋል።

ኤድስ የሕብረተሰብ የጤና ጠንቅ መሆኑ እንዲያከትም ማድረግ ይቻላል ያለው የመንግሥታቱ ድርጅት የኤድስ ኤጀንሲ፤ ይህ የሚሆነው ግን በማስረጃ ላይ የተመሰረት የመካላከልና ሕክምና ስርዓት መገንባት፣ የሲቪል ማህበረሰቡን አቅም ማጎልበት እንዲሁም ማግለልና መድሎን መቅረፍ ከተቻለ ነው ብሏል።

ኤጀንሲው አክሎም የኤድስ ወረርሽን ማስቆም የዓለም መሪዎችን ጽናት እንደሚፈልግ ጠቅሶ፤ ጉዳዩ ከኹሉም በላይ የፖለቲካ እና የፋይናንስ ምርጫ መሆኑን ጠቁሟል።

ኤድስን የሚያስቆም መንገድ ላይ ገና አልደረስንም የሚለው ኤጄንሲው፤ ነገር ግን መንገዱን ለመከተል አሁን መወሰን እንችላለን ሲል ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤድስ በፈረንጆች 2030 የማህበረስብ የጤና ጠንቅ መሆኑ እንዲያበቃ ከስምንት ዓመት በፊት ግብ ነድፎ እየሰራ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።

ሆኖም ወረርሽኙን ለማስቆም ከሚረዱ ምክንያቶች አንዱ የተጠና የኢንቨስትመንት ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ነው የተባለ ሲሆን፤ በዚህም የበሽታው አምጭ በሆነው ኤችአይቪ ቫይረስ ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሱ አገራት፣ ወረርሽኙን ከመግታት አንጻር የተሻለ ውጤት ማስመዝገባቸው ነው የተገለጸው።

በምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ከፈረንጆች 2010 ጀምሮ አዳዲስ የኤችአይቪ ስርጭት በ57 በመቶ መቀነሱም ተጠቅሷል።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው መያዛቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ይህ ቁጥር በ1995 ከነበረው በበሽታው የመያዝ ቁጥር በ59 በመቶ ቀንሷል ነው የተባለው።

ከኤድስ ጋር በተገናኘ የሚፈጠር ሞት በፈረንጆች 2004 ከነበረው ምጣኔ በዚህ ወቅት በ69 በመቶ መቀነሱን ኤጄንሲው ባለፈው ሐሙስ ዕለት ይፋ ያደረገው ሪፖርት ያመለክታል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ 39 ሚሊዮን ሰዎች ከቫይረሱ ጋር ይኖራሉ የተባለ ሲሆን፤ የበሽታው ስርጭት ጾታቸውን በሚቀይሩ ሰዎች ላይ በ14 እጥፍ፣ በግብረሰዶማውያን ወንዶች ላይ በ11 እጥፍ፣ ዕጽ በሚጠቁሙ ሰዎች ላይ ደግሞ በሰባት እጥፍ እንዲሁም በሴተኛ አዳሪዎች ላይ በአራት እጥፍ የበለጠ መሆኑ ተጠቁሟል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here