በኢትዮጵያ የሕጻናት ማረሚያ ቤት አንድ ብቻ መሆኑ በታዳጊዎቹ ላይ ከፍተኛ የስነልቦና ጉዳት እያደረሰ ነው ተባለ

0
425

በኢትዮጵያ የሕጻናት ማረሚያ ቤት አንድ ብቻ መሆኑ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ ተወስደው በሚታረሙ ታዳጊ ታራሚዎች ላይ ከፍተኛ የስነልቦና ጉዳት እያደረሰ መሆኑን የአዲሰ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ሕጻናት ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

በአዲሰ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ሕጻናት ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በወንጀል ነክ ነገር ገብተው የተገኙ ሕጻናት ማቆያ ተሃድሶ ተቋማ ሥራ አስኪያጅ እንግዳው መንግሥቱ፤ ‹‹ሕጻናት በሚሰሩት የወንጀል ድርጊት ምክንያት ከወላጆቻቸው ተነጥለው አዲስ አበባ ወደሚገኘው ማረሚያ ቤት ሲመጡ ብቸኝነት እንደሚሰማቸውና በነገ ማንነታቸው ላይም ቀላል የማይባል ጫና እንደሚያሳርፍ ገልጸዋል፡፡

ክልሎች በራሳቸው አቅም የሕጻናት ማረሚያ ተቋም እንዲገነቡ በተደጋጋሚ ቢነገራቸውም እስካሁን የገነባ ክልል የለም ሲሉም ተደምጠዋል።

ለአብነትም በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ለታዳጊዎች ማረሚያ ቤት ተብሎ በ2011 ተገንብቶ የነበረ ቢሆንም፣ ከታለመለት ዓላማ ውጭ የፍትህ ቢሮ አድርገውታል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም በወንጀል በሚሳተፉ ሕጻናት ላይ የሚሰጠው የፍርድ ውሳኔ እንደአዋቂዎች ረዥም ዓመት መሆኑ ሌላኛው በታዳጊዎች ላይ የስነልቦና ጫና የሚያደርስ ጉዳይ መሆኑ ገልጸዋል።

በዚህም በማረሚያ ቤቱ ከአንድ ዓመት በላይ በሚቆዩ እና የፍርድ ሂደታቸው እንደአዋቂ ታራሚዎች እስከ 15 አመት ተፈርዶባቸው በሚታረሙ ታዳጊዎች ላይ ከፍተኛ የስነልቦና ጉዳት እያደረሰ ነው ብለዋል፡፡

ወደ ማረሚያ ቤቱ የሚገቡት ሕጻናት ከዘጠኝ እስከ 18 ዓመት የሆናቸው ታዳጊዎች ብቻ መሆናቸውን የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ፣ በ2015 ብቻ 390 ሕጻናት ወደ ማረሚያ ቤቱ መግባታቸውን ተናግረዋል።

ወደ ማረሚያ ቤቱ የሚገቡት ታዳጊዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እንደሚጨመር ጠቁመውም፣ ከሚገቡት ሕጻናት አብዛኞቹ ከደቡብ እና ኦሮሚያ ክልሎች የመጡ መሆኑን አስረድተዋል።

ሕጻናቱ የሚፈጽሙት ወንጀል በዋነኝነት አስገድዶ መድፈር፤ ግብረ ሰዶምና የስረቆት ወንጅል እንደሆነ ጠቅሰው፣ እንደ ወንጀሉ ክብደትና ቅልለት ከአንድ እስከ 15 ዓመት የተፈረደባቸው ታዳጊዎች መኖራቸውን ነው የገለጹት።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here