በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን፣ ሽሬ ከተማ የጣለው ከባድ ዝናብ ከ210 ሺሕ በላይ የሚሆን የተፈናቃዮችን መጠለያ ጣቢያ ማውደሙን የዞኑ አስተዳደር ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
የሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ተክላይ ገብረመድኅን ከሐምሌ ወር መግቢያ ጀምሮ ባልተለመደ መልኩ እጅግ ከፍተኛ የዝናብ መጠን ሲጥል እንደነበር ገልጸው፣ በተለይ ከባለፈው ሰኞ ዕለት ጀምሮ የጣለው ከባድ ዝናብ የተፈናቃዮችን መጠለያ ማውደሙን ተናግረዋል።
ይህን ተከትሎም በሽሬ ከተማ የሚገኙ 18 የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን ነው የገለጹት።
በከተማው ካሉ ከ360 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች ከስልሳ በመቶ በላይ የሚሆኑት በፕላስቲክ እና ሸራ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ መሆናቸውን ጠቁመው፣ የጣለው ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ እነዚህን የፕላስቲክ እና ሸራ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ማውደሙን ገልጸዋል።
አስተዳዳሪው አክለውም ሰኞ ሐምሌ 10/2015 በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ሳቢያ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ተፈናቃዮች መሞታቸው እና የሴቷ አስከሬን እስካሁን አለመገኘቱን ተናግረዋል፡፡
በአንድ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ቢያንስ ከ40 ሺሕ በላይ ሰዎች እንደሚኖሩ የተገለጸ ሲሆን፣ በጎርፍ አደጋው ምክንያት ጣቢያዎች ከወደሙ በኋላ፣አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ውጭ እንደሚያድሩ እንዲሁም ብርድ እና ውርጭ እየተፈራረቀባቸው እጅግ አሳዛኝ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተጠቁሟል።
እንዲሁም የጣለው ከባድ ዝናብ መጠኑ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑም የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ሞልተው ወደ ከተማው ነዋሪ ቤት ጭምር በመግባት በእንሰሳት እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱም ተሰምቷል፡፡
ለተፈናቃዮች እየቀረበ ያለው የሰብአዊ ድጋፍ ዝቅትኛ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ መልሶ የማቋቋም ሥራውን ፈታኝ ካደረጉት ነገሮች መካከልም በተለይ ከአዲ አሮ ተፈናቅለው የመጡ ተፈናቃዮች ቦታ አሁንም ድረስ በኤርትራ ሠራዊት ቁጥጥር ስር የሚገኝ መሆኑ ነው ተብሏል።
በክልሉ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ወደቦታቸው መመለስ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አንድ አካል ቢሆንም፣ እስካሁን አንድም ከመጠለያ ጣቢያ ወጥቶ ወደ ቀደመ መኖሪያው የተመለሰ ሰው አለመኖሩ ተገልጿል።
ስለሆነም የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ለተፈናቃዮቹ አስፈላጊውን ትኩረት ሰጥቶ ወደቀያቸው የመመለሱን ሥራ እንዲሰራ እና የሚደርሰው አደጋም ከዚህ በላይ የከፋ እንዳይሆን የዞኑ አስተዳዳሪ ጠይቀዋል፡፡



