በጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ በአኝዋክ እና በኑዌር ብሔር አባላት መካከል በተነሳ ግጭት ከኹለቱም ብሔሮች ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የከተማው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ግጭቱ የተቀሰቀሰው ትናንት ሐምሌ 11/2015 ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ መሆኑን የተናገሩት ነዋሪዎቹ፤ እሁድ ሐምሌ 09/2015 የአኝዋክ ብሔረሰብ ተወላጅ የሆነ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የኹለተኛ ዓመት ተማሪ በኑዌር ብሔር አባላት መገደሉን ተከትሎ፣ በኹለቱ ብሔር አባላት መካከል ግጭት መቀስቀሱን ጠቅሰዋል።
በክልሉ የብሔር ብሔርሰቦች ቀን መከበር ከጀመረበት ከ2008 ወዲህ ለኹሉም ብሔር ብሔረሰቦች መገለጫ ይሆናል ተብሎ የታሰበ አንድ ቤት በጋምቤላ ከተማ የአኝዋክ ብሔረሰብ አባላት በብዛት በሚኖሩበት አካባቢ መሰራቱን ተክትሎ፤ የኑዌር ብሔረሰቦች በአካባቢው መስፈር ከጀመሩ ወዲህ በኹለቱ ብሔረሰቦች መካከል በየጊዜው ግጭት እንደሚፈጠር ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት።
ስለሆነም የአኝዋክ ብሔረሰብ ተወላጅ የሆነው የዩኒቨርሲቲ ተማሪው ባለፈው እሁድ ዕለት ከተገደለ በኋላም፤ የኑዌር ብሔረሰቦች አካባቢውን ለቀው ይውጡ በሚል ከትናንት ሐምሌ 11/2015 ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽት ኹለት ሰዓት ድረስ በኹለቱ ብሔር አባላት መካከል ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
የአኝዋክ ብሔር አባላት የኑዌር ብሔር አባላትን “ሰፈራችንን ለቃችሁ ውጡልን” ሲሉ፤ የኑዌር ብሔር አባላት በበኩላቸው፣ “ከባሮ ወንዝ ወዲህ ያለው የእኛ እንጂ የእናንተ አይደለም” እንደሚሉም መረዳት ተችሏል።
ይህን ተከትሎም በዛሬው ዕለት በጋምቤላ ከተማ ባንኮችን ጨምሮ ኹሉም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች መዘጋታቸው እንዲሁም የተሽከርካሪ እና የሰው እንቅስቃሴ አለመኖሩም ተጠቁሟል።
ከዛሬ ረፋድ ጀምሮ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ ከተማው መግባታቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
የጋምቤላ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኡገቱ አዲንግ፤ “ችግሩ ከባድ በመሆኑ በመንግሥት በኩል ፈቃድ እስካላገኘን ድረስ መረጃ አንሰጥም” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።



