በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መርሃቤቴ ወረዳ ዓለም ከተማ ባለፈው አርብ ሐምሌ14/2015 የመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት አባላቱ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው በዕለቱ ጠዋት 12 ሰዓት ገደማ ትጥቅ አስቀምጠው ስፖርት በመስራት ላይ ሳሉ ነው ተብሏል።
በዚህም ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የሠራዊቱ አባላት መገደላቸው እና መቁሰላቸው ነው የተነገረው።
ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የከተማው ነዋሪ፣ ጥቃቱን የፈጸሙት የፋኖ ታጣቂዎች መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ከአምስት እስከ 15 የሚደርሱ የሠራዊቱ አባላት ሳይሞቱ እንዳልቀረ ሲወራ መስማታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የመከላከያ ሠራዊት አባላት በከባድ መሳሪያ የታገዘ የአጻፋ የተኩስ እርምጃ በፋኖ አባላት ላይ መክፈታቸውንና ከሦስት በላይ የፋኖ አባላት ሳይገደሉ እንዳልቀሩም ከነዋሪዎቹ መረዳት ተችሏል።
በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ አባላት መካከል ለአንድ ሰዓት ያህል የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድ ከቆየ በኋላም፤ የፋኖ አባላት አካባቢውን ለቀው ሸሽተዋል ነው የተባለው።
የመከላከያ ሠራዊት አባላት ዓለም ከተማ አቅራቢያ ገምሹ በተባለ ቦታ እና በመርሃቤቴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ካመፕ እንዳላቸውና በአካባቢው በብዛት ከሚንቀሳቀሱ የፋኖ አባላት ጋር አለመግባባት መፈጠሩ ተመላክቷል።
ከዚህ ቀደምም በኹለቱ ኃይሎች መካከል በአካባቢው ተደጋጋሚ የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ ነበር ተብሏል።
በአማራ ክልል በቡድን ተደራጅተው በሕገወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች አሉ በሚል የክልሉ አስተዳደር እና የፌደራል መንግሥት ሕግ ማስከበር ያሉትን ዘመቻ እያካሄዱ ይገኛል።
ይህን ተከትሎም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያዎች እየተካሄዱ ሲሆን፣ የመንግሥት አመራሮች፣ የጸጥታ ኃይል አባላት እና የንጹሃን ሞትም በየጊዜው ይመዘገባል።



