በአዲስ አበባ የመንግሥት ሠራተኞች በፈረቃ እንዲሰሩ ዝግጅት እየተደረገ ነው

0
472

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች በፈረቃ ለመስራት የሚፈልጉትን የሥራ ፈረቃ መርጠው ለፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ ማስገባታቸውን አዲስ ማለዳ ከሠራተኞች ሰምታለች።

በከተማ አስተዳደሩ ስር በሚገኙ የመንግሥት ተቋማት የሚሰሩ ሠራተኞ በፈረቃ እንዲሰሩ የተፈለገበት ዋነኛ ምክንያት፣ መንግሥት ለሠራተኞች ደመወዝ እንደማይጨምር ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ማስታውቁን ተከተሎ የትርፍ ሰዓት ሥራ በመስራት ገቢያቸውን ይሚደጉሙበት አሰራር እንዲኖር በዝግጅት ላይ መሆኑን ለማወቅ ትችሏል።

የሥራ ፈረቃ ዝግጅቱ የሠራተኞችን የግል ገቢ ለማሳደግ ከማገዝ ባለፈ፣ ተገልጋዮች ሙሉ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል በሚል እንደሆነም ተጠቁሟል።

ሆኖም የሥራ ፈረቃው በአዲሱ በጀት ዓመት ይጀመራል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን አለመጀመሩ እና መቼ ሊጀምር እንደሚችልም የተገለጸ ነገር አለመኖሩን ሠራተኞቹ ገልጸዋል።

ከሐምሌ 01/2015 ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል በሚል ባለፈው ሰኔ ወር ኹሉም ሠራተኞች ከቀረቡ ሦስት አማራጭ የሥራ ፈረቃዎች የሚፈልጉትን ሞልተው እንዲያስገቡ ቢደረግም እስካሁን አልተጀምረም ነው የተባለው።

ሥሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ ሠራተኛ ባለፈው ሰኔ ወር “በየሥራ ሂደታችሁ ቅጽሞ ልታችሁ ቶሎ ላኩ” በመባሉ ተሞልቶ መላኩን ገልጸው፣ ሆኖም ከሐምሌ 01/2015 ጀምሮ የሥራ ፈረቃው ይጀመራል ብሎ ኹሉም ሠራተኛ እየጠበቀ የነበረ ቢሆንም እስካሁን አልተጀመረም፣ በጉዳዩ ላይም ምላሽ የሰጠ አካል የለም ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ በየተቋማቱ ሠራተኞቹና አስተዳደር አካላት ውይይት ማድረጋቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ በጠዋት ለሚገቡና አምሽተው ለሚወጡ ሠራተኞች የትራንስፖርት እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል እና የደህንነት ስጋት መኖሩንም ሠራተኞች በጥያቄ ማቅረባቸው ተመላክቷል።

ዕቅዱ ተግባራዊ የሚደረገው ተገልጋይ በሚበዛባቸው በከተማ አስተዳደሩ ሥር በሚገኙ የተመረጡ የመንግሥት ተቋማት ላይ እንደሆነ ሠራተኞች ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሶ፣ በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች የአመራርና የሠራተኛ ውይይት መካሄዱን ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

ቢሮው የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ ፈረቃው ከሐምሌ 01/2015 ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል አላልኩም ያለ ሲሆን፣ መቼ ተግባራዊ እንደሚሆንም አይታወቅም ብሏል።

በጉዳዩ ላይ በተደረጉ ውይይቶች የጸጥታ፣ የትራንስፖርት፣ የሰው ኃይል እንዲሁም የአከራይ ተከራይ ጉዳይ መነሳታቸውን በመጠቆምም፣ እነዚህን ጉዳዮች መነሻ በማድረግ ወደ ጥናት መገባቱን ነው የገለጸው።

ሠራተኞች በፈረቃ እንዲሰሩ ያስፈለገበትን ምክንያት ከመግለጽ የተቆጠበው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ፣ የጥናቱ ውጤት ታይቶ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ጠቁሟል።

ከዚህ ቀደም ከተማ አስተዳደሩ ሰራተኞች 16 ሰዓት በመስራት ህዝብን በይበልጥ ለማገልገል ማሰቡን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here